ከ40ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገፅ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በፍኖተ ሰላም የአየር ላይ ጥቃት በመፈጸም ከሶስት አመት በታች ያሉ ህጻናትን ጨምሮ 270 ንፁሀን ዜጎችን ገድሏል በሚል ይህን  ምስል  በስፋት አጋርቷል

ይህ ጽሁፍ እስከሚታተምበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ ​​​​ 7000 ጊዜ ያህል በመታየት  ከ 300 በላይ ግብረመልሶችን አግኝቷል።

የፌድራል መንግስት እና በአማራ ክልል  በፋኖ ሚሊሻ ቡድኖች መካከል ግጭት እንዳለ ይታወቃል። ይህ ግጭት የተፈጠረው መንግስት የክልሉ የልዩ ሃይሎች ትጥቅ ፈትተው ከሌሎች የጸጥታ አደረጃጀቶች  ማለትም መክላክያ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም የክልል ፖሊስ ተቋማት ጋር እንዲዋሃዱ ባዘዘ ጊዜ ነው።

በአማራ ክልል እነዚህ የታጠቁ ሚሊሻዎች በርካታ አካባቢዎች ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በክልሉ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

እ.ኤ.አ. ነሀሴ 11 ቀን 2023 የወጡ ዘገባዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፎች በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት በርካታ ጉዳቶች መከሰታቸውን ይጠቁማሉ።

መንግስት በፋኖ ታጣቂዎች ጋር ባደረገው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ዋና ዋና ከተሞችን መልሶ መቆጣጠር ችሏል። ያም ሆኖ በክልሉ ግጭቶች እንደቀጠሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህ በፌስቡክ የተጋራው ፎቶ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም በተባለ ቦታ ላይ ጥቃት አድርሶ 270 ንጹሃንን  እንደገደለ ለማሳየት የቀረበ ነው። ይህ መረጃ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሀቅቼክ የጉግል ተገላቢጦሽ ምስል መፈለጊያን በመጠቀም ምስሉን መርምሯል። በዚህም ምስሉ ከዚህ በፊት በፌስቡክ ላይ የተለጠፈው በሀምሌ 21 ቀን 2023 መሆኑን አረጋግጧል።

በወቅቱ የተጋራው ይህ የፌስቡክ ፖስት የአውሮፕላኖቹን ብቃት  እንደሚያሳይ ከሚገልፅ ፅሁፍ ጋር ተጋርቶ ነበር። 

ስለዚህ ሀቅቼክ  በፍኖተስላም  የድሮን ጥቃት እንደነበረ እና ሰዎች እንደሞቱ የወጡ ዜናዎች ቢኖሩም፤ ነገር ግን ይህ የፌስቡክ ፖስት የቆየ ምስልን በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts