ከ150 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ግንቦት 23 ፤ 2014 ዓ.ም ላይ “ሰበር ዜና ‘ወያኔ ዘመነ ካሴ ኤርትራ በገባ ጊዜ እንዲህ የደካማ እናቱን ንብረት አላቃጠለም አልዘረፈም ነበር። ዛሬ የአብይ መንግስት በጭንቅ ጊዜ የራሱን ወንበር ብሎም ህዝብን የታደገውን የአርበኛ ዘመነ ካሴ እናት ልጅሽን አምጭ በማለት እንዲህ አውድሞታል።” የሚል ፅሁፍ በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። ዘመነ ካሴ የፋኖ መሪ እንደሆነ በተከታዎቹ ዘንድ የሚነገርለት ግለሰብ ነው።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከ 190 በላይ ግብረመልስ ሲያገኝ ከ65 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።  

ፋኖ ማለት ሀገር ለመጠበቅና ከጠላት ለመከላከል በበጎ ፈቃድኝነት የተሰባሰቡ የአማራ ወጣቶች የወል ስም ነው። በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳውን ጦርነት የትግራይ ኃይሎች በአጎራባች የአማራና የአፋር አካባቢዎች ባደረጉት መስፋፋት መንግስት ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው አያሌ የፋኖ አባላት ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል። በመንግስት በራሱ የታጠቁት የፋኖ አባላትም የህወሓት ኃይሎች የአማራን እና የአፋርን አካባቢዎችን ለቀው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፈው በውጊያ ተሳትፈዋል።

ታህሳስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ ካሉ የትግራይ አካባቢዎች ለቀው መወጣታቸውን እና ከ13 ወራት ቆይታ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ መወሰናቸውን አስታውቀዋል። 

መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም የፌደራሉ መንግስት በትግራይ የተኩስ አቁም ስምምነት [ለሰብዓዊ እርዳታ ሲባል]አድርጓል።  በሰብዓዊ እርዳታ እጥረት ምክንያት ለሚጠፋው የሰው ልጅ ህይወትን ለመታደግ የፌደራሉ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታን ግምት ውስጥ ያስገባ ተኩስ አቁም እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።

ይህን ተከትሎ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰጠው መግለጫ “በአማራ ክልል ውስጥ ሁከት ፣ ብጥብጥ እና ስርዓት አልበኝነት በማስፈን ሕዝብ እንዳይረጋጋ እርስ በርሱ እንዲጋጭና አንድነቱን እንዲያጣ የሚያደርጉ ተግባራት በመፈፀም ራሳቸውን በአማራ ህዝብ ጉያ ውስጥ የወሸቁ ጠላቶችን ለማስቆም ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልፆ፣ እየተከናወነ ለሚገኘው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ መንግስታዊ ተግባር በዓላማው፣ በሂደቱም ሆነ በውጤቱ የሕዝብ እና የሀገር ደኅነነትን ለማረጋገጥ የታለመ መሆኑን በመገንዘብ መላው የአማራ ህዝብ ሕግ እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት ሙሉ ውግንናውን በመስጠት ውስጣዊ አንድነቱን አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ” ገልጿል።

ከዚህ በኋላ የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አካውንቶች እና ድረ-ገፆች በፌደራል መንግስቱ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንዳለ የሚያሳይ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ነበር።  

እንደ ዋዜማ ሬድዮ ዘገባ ከሆነ የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የፋኖ አመራር በመንግስት መታሰሩን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎች እና በፊደራሉ መንግስት መካከል ግጭት ተከስቶ ነበር።   

የክልሉ መንግስት በበኩሉ ሁኔታውን የህግ ማስከበር ሂደት ነው በማለት ምላሽ የሰጠ ሲሆን ሁኔታው ክልሉን ለመረበሽ በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች እንደተፈጠረ ገልጿል። የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ይልቃል ከፍያለ “መንግስት ፋኖን ማጥቃትም ሆነ ትጥቅ የማስፈታት አላማ እንደሌለው በማስረዳት ዘመቻው ትኩረት ያደረገው በክልሉ በህገወጥ የመሳርያ ዝውውር በግድያ እና በዝርፍያ የሚሳተፉ ሀይሎችን እንደሆነ ገልፀው ነበር። 

ይህ በእንዲህ እያለ መንግስት የፌደራል እና የክልል የፀጥታ አካላት በፋኖ አመራሮች ቤት በመግባት ማሰር እንደጀመሩ የሚናገሩ የተለያዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።    

ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም My views on news የተባለ ድረ-ገፅ “ፋኖ ዘመነ ካሴ የፌደራል መንግስቱን አስጠነቀቀ” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ አስነብቦ ነበር።

የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶችም የፋኖ ዘመነ ካሴ ቤተሰብ ቤቶች እና ንብረቶች እንደወደሙ እና እንደተቃጠሉ ሲገልፁ ቆይተዋል። አንድ ከ180 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ “የዘመነ ካሴ ወንድም ንብረት ካሴ የ85 አመት እድሜ ያላቸው እናታቸው ቤትና ንብረት በመንግስት ታጣቂዎች እንደወደመ ገልጿል” በማለት መረጃውን አጋርቶ ነበር።   

ሀቅቼክ ያገኘው የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሁኔታ ተገን በማድረግ የተለጠፈ ነበር። 

ሀቅቼክ ምስሉን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሉን ከ3 የተለያዩ ምስሎች ጋር ቀደም ባለ ጊዜ ተጋርቶ አግኝቶታል። ምስሉ ከዚህ ቀደም ጥር 15 ቀን ከ13ሺ በላይ ተከታይ ባለው የትዊተር አካውንት ላይ “ከአባይ ተሻግረው የመጡ ታጣቂዎች በሆሮ ጉድሩ ዞን የኦሮሞ ገበሬ ቤቶችን አቃጥለዋል” በሚል ርዕስ ተለጥፎ ነበር። 

የፋኖ ዘመነ ካሴ እናት ቤት እንደተቃጠለ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም ይህ የፌስቡክ ፔጅ የተጠቀመው ምስል መረጃው በፌስቡክ ገፁ ከተጋራበት ጊዜ እጅግ ቀደም ብሎ የተላለፈና የተባለውን ዜና የማይደግፍና የተሳሳተ እንደሆነ ታውቋል።
ስለዚህ ሀቅቼክ መረጃውን ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋለውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል።      

Similar Posts