በ30 ታህሳስ 2013 ዓ.ም ደሃይ ውቅሮን ትግራይን የተባለ ከ1,950 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ ከዚህ በታች ያለውን ብዙ ወታደሮችን የጫኑ የጭነት መኪናዎችን እና በመንገድ ዳር ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚያሳየው ምስል የፌደራል ወታደሮች መሆናቸውን እና በህወሃት ሀይሎች ላይ እየተካሄደ ላለው ወታደራዊ ዘመቻ ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ እየገቡ መሆናቸውን ገልፆ አጋርቷል። በትግርኛ የተፃፈው ጽሑፍ “እባክዎን ይህንን አስቸኳይ መረጃ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት እንዲያየው አጋሩ። [አብይ አህመድ] ብዙ በወታደሮች  የጫኑ የጭነት መኪናዎች ወደ ትግራይ ከተሞች እየላከ ነው” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ልጥፉን መርምሮ ከዚህ በታች ያለው ምስል ወደ ትግራይ የተላኩት የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደማያሳይ እና መረጃው ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስት እና በህወሃት የሚመራው የትግራይ ልዩ ፖሊስና በፌደራል መንግስት ሀይሎች መካከል ከ25 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ግጭት የተከሰተ ሲሆን በክልሉ ውስጥ ለሦስት ሳምንታት ያህል ከተካሄደ ውጊያ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኃይሎች መቐለ፣ ሽሬ፣ አዲግራት፣ አክሱም እና ሌሎችንም በትግራይ ክልል የሚገኙ ከተሞችን መቆጣጠሩን መንግስት መግለፁ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በኋላ የፌደራል መከላከያ ሰራዊቱ እና የፌደራል ፖሊስ ኃይል በጋራ ባደረጉት ዘመቻ በ30 ታህሳስ 2013 ዓ.ም ስብሃት ነጋን እና በ2 ጥር 2013 ዓ.ም የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩትን አባይ ወልዱን ጨምሮ ከፍተኛ የሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች መገደላቸው እና በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልፁአል

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰው የፌስቡክ ልጥፍ ቢሰራጭም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባል የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ከሆነ በፌስቡክ ልጥፉ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል በትግራይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ወደ ትግራይ እየሄዱ የሚገኙ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን አያሳይም። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በ9 ግንቦት 2009 ዓ.ም  The World (ዘ ወርልድ) በተባለ የአሜሪካን ዲጂታል ሚዲያ ድረ ገጽ ላይ ሲሆን በምስሉ ላይ የሚታዩት ወታደሮች በ4 ሰኔ 1990 ዓ.ም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ዛላምበሳ ግንባር በሚወስደው መንገድ ላይ ያልፉ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን የሚያሳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። 

እውነት ነው በፌደራል መከላከያ ሰራዊት እና በህወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይሎች መካከል በትግራይ ውስጥ ግጭት እና አለመረጋጋት ነበር። ሆኖም ሀቅቼክ መረጃውን መርምሮ በልጥፉ ላይ የሚታየው ምስል ወታደራዊ ዘመቻ በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ትግራይ ሲገቡ የማያሳይ በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። .

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Similar Posts