አንድ የዩቲዩብ ቻናል በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም ህወሓት ከኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት ጋር ድርድር እንደማይፈልግ ገለፀ በሚል ርዕስ አንድ ቪድዮ አጋርቶ ነበር።

ሆኖም ቪድዮው ሲጫወት ያለው መልዕክት ህወሓት ያስቀመጣቸው አምስት የቅድመ ድርድር ነጥቦች እንዳሉ ይናገራል። የቪድዮው ርዕስ እና የሽፋን ምስል ህወሓት ድርድር እንደማይፈልግ የሚያስቀምጥ ቢሆንም የቪድዮው ይዘት ግን ህወሓት ለድርድሩ ያስቀመጣቸውን አምስት ቅድመ ሁኔታዎች ይናገራል። 

በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ የዩቲዩብ ቪድዮው ያስተላለፈውን መልዕክት መርምሮ አሳሳች ብሎታል።

የፌደራል መንግስት እና ህወሓት እስካሁን ድረስ መፍትሄ ባላገኘ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። 

በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ሁለቱ ተዋጊ ሀይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት [ለሰብዓዊ እርዳታ] ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ከዚያን በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ እየተሻሻለ መቷል።   

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል ቀጥተኛ ንግግሮች እንደተደረጉ የሚያሳዩ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የፌደራል መንግስቱ ከህወሓት ጋር ድርድሮችን ሊያደርግ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ባለፈው ሳምንት ለ ሞንድ የተባለ የፈረንሳይ ጋዜጣ በድረ-ገጹ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር በግንቦት ወር መጨረሻ አካባቢ በታንዛኒያ አሩሻ ድርድር ሊያደርጉ እቅድ እንደተያዘ የሚገልፅ ፅሁፍ አስነብቧል። 

ይህ የፈረንሳይ ጋዜጣ ከተለያዩ የዲፕሎማት ምንጮቼ አግኝቼዋለው ባለው መረጃ መሰረት ህወሓት በምዕራብ ትግራይ ድንበር አካባቢ ላይ ያሉ ቦታዎች ላይ የሚያነሳውን የባለቤትነት ጥያቄ ትቶታል ብሎ ዘግቧል።   

ሆኖም ህወሓት ውዝግብ የተፈጠረባቸው የምዕራብ ትግራይ ቦታዎች ላይ ያለውን ጥያቄ ትቶታል የሚለው መረጃ ውሸት እንደሆነ አስታውቋል። 

ይህን ተከትሎ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለተለያዩ አካላት በፃፉት ግልፅ ደብዳቤ የሰላም ድርድር ለማድረግ ወደ ኬንያ ናይሮቢ የትግራይ ተወካዮችን እንደሚልኩ አስታውቋል። በአንፃሩ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ የፌደራሉ መንግስት ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ እንዳዘጋጀም ተናግረዋል። 

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ሆኑ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ምስጢራዊ ውይይትም ሆነ ድርድር እንዳልተደረገ ገልፀዋል። 

ህወሓት በቅርብ በሰጠው መግለጫ በድርድሩ እንዲጠበቁለት የሚፈልጋቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል። ከነዚህም መካከል የምዕራብ ትግራይ ቦታዎች ጉዳይ፣ የሪፈረንደም ህዝበ ውሳኔ፣ የጦር ኃይሉን ይዞ መቀጠል እና በትግራይ ለተፈጠረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት የሚሉትን አስቀምጧል።

ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም የህወሓት አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በትዊተር አካውንታቸው ህወሓት አልደራደርባቸውም የሚላቸውን አምስት ነጥቦች አስፍረዋል።         

ቪድዮው ይህን ሁኔታ ተገን በማድረግ የተለቀቀ ሲሆን በዚድዮው የተላለፈው መልዕክት ይዘት ህወሓት ለድርድር ስላስቀመጣቸው አምስት ነጥቦች ሆኖ ሳለ በቪድዮው ሽፋንና ርዕስ የተቀመጠው ምስልና ህወሓት ድርድር እንደማይፈልግ የሚገልፀው ርዕስ አሳሳች ያደርገዋል። 

በተጨማሪም ሀቅቼክ ህወሓት ከፌደራል መንግስት ጋር ለመደራደር የቅድመ ድርድር ነጥቦቹን እንዳስቀመጠ እንጂ ድርድር እንደማይፈልግ እንዳልገለፀ አጣርቷል። ስለዚህ ሀቅቼክ በዩቲዩብ ቪድዮው ሽፋኑ እና ርዕስ እንዲሁም በውስጥ ይዘቱ መልዕክት መካከል ያለውን ግንኙነት አጣርቶ አሳሳች ብሎታል።

Similar Posts