አንድ በዩቲዩብ የተሰራጨ ቪድዮ በፊት ገፁ ላይ “ህወሓት አውሮፕላን አገተ” በሚል ርዕስ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም መረጃ አጋርቶ ነበር። ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ ቪድዮ ከ2500 በላይ እይታ ማግኘት ችሏል።

ሀቅቼክ ሙሉ ቪድዮውን በመመልከት ቪድዮው በውስጡ ህወሓት አውሮፕላን እንዳገተ የሚገልፅ ምንም አይነት መረጃ እንደሌለው የተገነዘበ ሲሆን በአንፃሩ ህወሓት አውሮፕላን መቀሌ እንዳያርፍ መከልከሉን ይናገራል። 

ስለዚህ ሀቅቼክ በዚህ የዩቲዩብ ቪድዮ የተላለፈውን መረጃ አሳሳች ብሎታል።  

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል የተጀመረው ጦርነት እስካሁን ድረስ ማብቂያ አላገኘም።   

ከመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱ ተዋጊ ሀይሎች መካከል ለሰባዊ እርዳታ በሚል በተፈጠረው የተኩስ አቁም ስምምነት የሰብዓዊ እርዳታ ፍሰቱን እንዳሻሻለው ተነግሯል።    

ይህ በእንዲህ እንዳለ በህወሓት አመራሮች እና በፌደራል መንግስት መካከል ቀጥተኛ ውይይቶች እንደነበሩ የሚዘግቡ ያለተረጋገጡ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ድርድር እና ውይይት ለማድረግ እንደተቃረቡ የሚያሳዩ አንዳንድ መረጃዎች እየተሰሙ ነው። 

የህወሓት አመራር የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በፃፉት ግልፅ ደብዳቤ አማካኝነት አስተዳደራቸው ሰላም ለማውረድ ለሚደረገው ድርድር ተወካዮቻቸውን ወደ ናይሮቢ ኬንያ እንደሚልኩ ገልፀዋል።   

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በተገኙበት መድረክ የፌደራሉ መንግስት ከህወሓት ጋር ለሚደረግው ድርድር ኮሚቴ ማዋቀሩን ገልፀዋል። 

በሌላ መልኩ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የሰብዓዊ እርዳታ እና መጓጓዣ መንገዶችን አስመልክቶ ይሚነሱ አንዳንድ ውዝግቦች ተስተውለዋል። በዚህም የፌደራል መንግስት እና ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ማደናቀፍን አስመልክቶ እስር በእርስ ሲካሰሱ ቆይተዋል። 

ባለፈው መሰከረም ወር የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ወደ ትግራይ ከገቡት 445 የዕርዳታ መኪናዎች ውስጥ 407 የሚሆኑት መመለስ አንዳልቻሉ ገልጿል። በተመሳሳይ ሁኔታም ሰኔ 16 ፤ 2014 ዓ.ም ወደ ትግራይ ሲጓዙ የነበሩ የዕርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አየር ማረፍያ እንዳይወርዱ አግዷል በማለት የፌደራል መንግስት ህወሓትን ከሷል። ህወሓት ለፌደራል መንግስት ክስ አየር መንገዱ በነዳጅ እጥረት ምክንያት መስራት ማቆሙን በመግለፅ ምላሽ ሰጥቷል። 

የዩቲዩብ ቪድዮው የተጠቀሱትን ነባራዊ ሁኔታዎች ተገን በማድረግ እንደተጋራ መረዳት ይቻላል። ይህ የዩቲዩብ ቪድዮ “ህወሓት አውሮፕላን አገተ” በሚል ርዕስ ቪድዮውን ያጋራ ቢሆንም በቪድዪው የሚተላለፈው መልዕክት ህወሓት ወደ መቀሌ የሚደረጉትን በረራዎች በመከልከል የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ማስተጓጎሉን ይገልፃል። ይህም በፊት ገፁ ላይ ያለው ርዕስ እና በውስጥ ያለው መረጃ የማይገናኝ መሆኑን ያሳየናል።  ከነዚህ ምክንያቶች በተነሳ ሀቅቼክ ቪድዮውን መርምሮ አሳሳች ብሎታል። 

Similar Posts