ከ 70 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ግንቦት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ላይ “በርከት ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን መቀላቀላቸውን ሰምተናል” በሚል ፅሁፍ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።  

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከ200 በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ20 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል አጣርቶ ሀሰት ብሎታል። 

በፌደራል መንግስቱ ዘንድ ኦነግ ሸኔ እየተባለ የሚጠራው እና እራሱን ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ወታደራዊ ቡድን እስከ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወታደራዊ ክንፍ ነበር። ከዚያ በኋላ እራሱን ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተለይቶ የትጥቅ ትግልን አማራጩ አድርጓል። 

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የፌዴራሉ መንግስት ከኦነግ ሸኔ ጦር ጋር እያደረገ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ሁለቱ ሀይሎች ወደ ሰላማዊው የፖለቲካ ምህዳር እንዲገቡ ጠይቋል። በተጨማሪም መንግስት ለትግራይ ክልል የሰጠውን የሰላም አማራጭ [ተኩስ አቁም] ዕድል ኦነግ ሸኔንም በተመለከተ እንዲተገበረው ጠይቋል።

ቅዳሜ መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የደቡብ እዝ አመራር የሆኑት ኮሎኔል ግርማ አየለ በቡድኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ እንዳለ ገልፀው ነበር። የፌዴራሉ መንግስት ከክልል ሀይሎች ጋር ባደረገው ጥምረት የተቀናጀ ጥቃት በቡድኑ ላይ እያደረሰ እንደሆነ ኮሎኔሉ ገልፀው ቡድኑ ዘርፏቸው የነበሩ መሳሪያዎች ጥይቶች እና የመድሃኒት አቅርቦቶች እንደተማረኩም አስታውቀዋል።  

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል  በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሱ የተለያዩ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እና የአየር ጥቃቶች እንዳሉ የሚያሳዩ የተለያዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል። 

የመከላከያ ሰራዊት፤ የፌደራል ፖሊስ አባላት እና ሪፐብሊካን ጋርዶች በዘር በመከፋፈል ወደ ኦነግ ሸኔ እየተቀላቀሉ ነው የሚል የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶችም ተስተውለዋል።

ወደ ኦነግ ሸኔ የተቀላቀሉ የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት ሊንክ   

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በዘር እየተከፋፈሉ ኦነግ ሸኔን እየተቀላቀሉ ነው ሊንክ 

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህንን አጋጣሚ እና ሁኔታን መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።    

ሀቅቼክ ምስሉን ለማጣራት ጥረት ያደረገ ሲሆን ምስሉ ከዚህ በፊት ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ከ140 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገፅ ላይ የተጋራ ሲሆን ከፎቶው ጋር የተያያዘው መግለጫ ፅሁፍም እንዲህ ይነበበባል “የአብይ አህመድ መከላከያ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፈርሷል። በዚህም ከደሴ የተረፈው ኮምቦልቻ ከተማን ለቆ ወደ ከሚሴ ቢሄድም ከሚሴ ላይ ትጥቁን ለአካባቢው ህዝብ አስረክቦ ወደ መሀል ሀገር ለመሄድ፣ ማምለጫ መኪና አጥተው እየተንገላቱ ነው። እንደ አጋጣሚ ገንዘብ ያላቸው በኮንትራት መኪና ለሊት ወጥተው አምልጠዋል።” 

የፌደራል ሀይሎች መንግስትን ክደው ወደ ኦነግ ሸኔ እየተቀላቀሉ ነው የሚሉ የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶች ቢኖሩም የፌስቡክ ገፁ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመው ምስል የተሳሳተና የቀረበውን ሪፖርት የማያሳይ መሆኑ ታውቋል።

ይህም በመሆኑ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።  

Similar Posts