ከ100 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ መጋቢት 17 ቀን፣ “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ውሳኔ [ለሰብዓዊ እርዳታ ሲባል ተኩስ ማቆምን] ተከትሎ የኤርትራ ጦር ትግራይ ድንበር አካባቢ 13 ዘመናዊ ትጥቅ የታጠቀ ክፍለ ጦር ወደ ድንበር አስጠጋች” የሚል የፅሁፍ መግለጫ ያለው አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ1400 በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ 140 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።

ነገር ግን ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱ ፅሁፉን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል ትክክለኛነት አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።    

ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም መንግስት ከህወሓት ጋር አየተደራደረ ነው ተብሎ የሚናፈሰውን መረጃ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ “ስለ ድርድር ጉዳይ ብዙ ሲወራ ሰምቻለው ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ድርድር የሚባል ነገር የለም” በማለት ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም፣ “እስካሁን ድረስ ድርድር አላደረግንም ማለት እስከመጨረሻው ድረስ ንግግር(ድርድር) አናደርግም ማለት አይደለም ምክንያቱም ድርድር እና ንግግር ችግርን የመፍቻ አማራጮችን የምናይበት ነው” በማለት የመንግስትን አቋም አሳውቀዋል። 

መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም የፌደራሉ መንግስት አስቸኳይ እና አላማውን የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ላይ ያደረገ ግጭት ማቆም አውጇል። መንግስት በመግለጫው አንዳሳወቀው፣ ውሳኔው ወደትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ችግር ማድረስንና ህይወት ማዳንን ታሳቢ ያደረገ ነው። በመግለጫው መንግስት ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አማፂያኑ “ከማንኛውም የጦርነት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ እንዲሁም ከተቆጣጠሯቸው አጎራባች አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ” አንዱ ነው።

ይህንን የፌደራሉን መንግስት ውሳኔ ተከትሎ ህወሓት በበኩሉ የትኛውንም አይነት ግጭት ለማቆም ተስማምቷል። 

ነገር ግን ይህ የዕርቅ ውሳኔ በሂደት ላይ ባለበት ሰዓት የመከላከያ ሰራዊት ትግራይ ድንበሮች አካባቢ እየተጠጋ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች ወጥተዋል። ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሀሳብ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።   

ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት ጥረት ያደረገ ሲሆን ምስሉ ከዚህ ቀደም ሀምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም “ሳዋ-የብሄራዊ ቀን የብር እዮቤልዩ ክብረ በዓል” በሚል ርዕስ የታተመ ፅሁፍ አካል ሆኖ አግኝቶታል።  

ፅሁፉ ሳዋ ተብሎ የሚጠራው የኤርትራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የነበረውን የብር እዮቤልዩ ክብረ በዓልንና የ32ተኛ ዙር ምልምል ሰልጣኝ ወታደሮች የተመረቁበት ሁነትን በማስመልከት የቀረበ የዜና ሪፖርት ነበር። 

የኤርትራ ጦር በትግራይ ድንበር አካባቢ ሰፍሯል የሚሉ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም ይህ የፌስቡክ ፖስት ፅሁፉን ለመደገፍ የተጠቀመው ምስል የቆየ እና ከመረጃው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው ነው።

ይህም በመሆኑ የፌስቡክ ፖስቱ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል አጣርቶ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።     

Similar Posts