በጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከ290ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ “በጅማ ከተማ በአንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መኖርያ ቤት ውስጥ የተገኘ የጦር መሳርያ።” በማለት ሶስት ምስሎችን በማያያዝ አጋርቶ ነበር።
የመጀመርያው ምስል የተለያዩ ጠመንጃዎችን የሚያሳይ ሲሆን ሁለተኛው ምስል የጥይት እና የጦር መሳርያ ምስሎችን ያሳያል። ሶስተኛው ምስል ደግሞ የጦር መሳርያ የተገኘበትን ግለሰብ ምስል ያሳያል በማለት አጋርቶት ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ የፌስቡክ ፖስት በምስሉ ላይ የተመለከተው ግለሰብ “በጅማ የማህበረ ቅዱሳን ማዕከል ሰብሳቢ እና የደብተራ መድሃንያለም ቤተክርስትያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ነው።” የሚል የመግለጫ ፅሁፍን አብሮ አያይዟል።
ይህ የፌስቡክ ፖስት በብዙ ስዎች ዘንድ ተጋርቶ የነበረ ሲሆን ከ400 በላይ ግብረ መልሶችን ማግኘት ችሏል።
ይሁን እንጂ ምስሎቹ የቆዩ ሲሆኑ በፌስቡክ ገፁ የቀረበውን መረጃ እንደማይደግፉ ሀቅቼክ ማረጋገጥ ችሏል።
በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ መረጃውን ሀሰት ብሎታል።
በጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሊቀ-ጳጳሳት ከቤተክርስትያኗ ሲኖዶስ እውቅና ውጭ የተለያዩ ጳጳሳትን ሾመዋል።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ እና ሁለት ሌሎች ጳጳሳት አንድ ላይ በመሆን ወደ 26 የሚጠጉ ኤጲስ-ቆጶሳትን በተለያዩ የኦሮሚያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሾመዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአቡነ ሳዊሮስ አማካኝነት ወደ 70 የሚጠጉ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ደብሮች ላይ ተመድበው ነበር።
ከዚህ ሁኔታ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባን በመጥራት ከቤተክርስትያኗ እውቅና ውጭ የተሾሙትን ጳጳሶች እና በሹመቱ ላይ የተሳተፉትን በሙሉ አውግዛለች።
ከዚህም በተጨማሪ የቤተክርስትያኗ ሲኖዶስ እነ አቡነ ሳዊሮስን እና ሌሎች ጳጳሳትን የቤተክርስትያኗን ቀኖና በመተላለፋቸው ምክንያት ከአባልነት አስወግዳቸዋለች።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ከቤትክርስትያኗ ተለይተው የወጡት ሊቀጳጳሳትም በበኩላቸው ወደ 12 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሊቀጳጳሳትን በማውገዝ ከአባልነትም ማገዳቸውን አስታውቀው ነበር።
በዚህ መረጃ ላይ በመመስረት በጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም አንድ የፌስቡክ ፖስት ሶስት ምስሎችን በማያያዝ “በጅማ የማህበረ ቅዱሳን ማዕከል ሰብሳቢ እና የደብተራ መድሃንያለም ቤተክርስትያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር በሆኑ ግለሰብ መኖርያ ቤት ውስጥ የጦር መሳርያ ተገኘ” በማለት አጋርቶ ነበር።
የመጀመርያዎቹ ሁለት ምስሎች እንደ ማስረጃነት የተለያዩ የጠመንጃ እና የጥይት ምስሎችን የሚያሳዩ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የግለሰቡን ምስል ያሳያል።
ጠመንጃዎች የሚታዩበት የመጀመርያው ምስል በጥቅምት 19 ቀን 2012 ዓ.ም በቢቢሲ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ላይ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የተለያዩ የጦር መሳርያ መያዙን በሚገልፅ ፅሁፍ ስር ተጋርቶ ተገኝቷል።
ሁለተኛው ምስል ደግሞ በመስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ የሀገር ውስጥ የዜና ሚድያ ላይ ከተጋራ ፅሁፍ ላይ የተወሰደ ነው። በዜናው ላይም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተለያዩ የጦር መሳርያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እደሚያሳይ ይገልፃል።
ሊንክ
በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱን ሀሰት ብሎታል።