አንድ ከ436,600 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ እንዲሁም ከ1,500 በላይ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት ላይ “ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትጋራው ድንበር አካባቢ በቁጥር በዛ ያሉ ወታደሮቿን አስፍራለች” በማለት በህዳር 21 ፤ 2014 ዓ.ም የተለያዩ ምስሎችን አጋርቶ ነበር። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል። 

በጥቅምት 2013 የፌደራል መንግስት ከህወኃት ጋር በገቡት ግጭት ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱን ወደ ሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ያንቀሳቀሰ ሲሆን ይህን አጋጣሚ ካርቱም ወታደሮቿን አልፋሽጋ በሚባለው አካባቢ ላይ ለማስፈር ተጠቅማበታለች። ይህን የሱዳን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ትንኮሳ ብሎ የፈረጀው ሲሆን ይህ አካባቢ ሱዳን ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር የሚጋሩት ቦታ ሲሆን ድንበሩ ለብዙ ዘመናት በኢትዮጵያ ስር የነበረ ነው። የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ሃይሎች አወዛጋቢ በሆነው ድንበር አካባቢ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በሱዳን ወታደሮች እና በአካባቢው በሰፈሩ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረውብኛል የሚሉ ክሶችን አቅርቧል።  

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሃይሎች በሱዳን ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሰዋል የሚለውን ክስ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን “ብዛት ያላቸው አማጽያን ባንዳዎች እና አሸባሪዎች በሱዳን በኩል ዘልቀው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሞከሩ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአካባቢው ሚሊሻ መክቶ ወደመጡበት መልሷቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የልጥፉን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የጉግል የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ ሂደትን ተጠቅሟል። 

የመጀመሪያው ምስል የተወሰደው በህዳር 2009 ዓ.ም የሱዳን ወታደሮች በሰሜኑ የሱዳን ክፍል አካባቢ ልምምድ ሲያረጉ የሚያሳይ ነው። 

ሁለተኛው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው በሚያዝያ 2 ፤ 2012 ዓ.ም በቻይንኛ ቋንቋ በሚቀረብ አንድ ድህረ-ገጽ ላይ ነበር።

ሶስተኛው ምስል የተወሰደው ከ14 ዓመት በፊት በS.Telliks አማካኝነት ሲሆን ምስሉ በህዳር 14 ፤ 2012 ዓ.ም በአንድ ድህረ-ገጽ ላይ ተለቆ ነበር። 

የመጨረሻው ምስል የተለቀቀው በሕዳር 12 ፤ 2014 ዓ.ም በአንድ የአረብኛ ድህረ-ገጽ ላይ “የሱዳን ወታደራዊ ጦር ከኢትዮጵይ ጋር አለ የሚባለውን ግጭት እንደማይቀበል አስታወቀ” በሚል ርዕስ ስር የቀረበ ነበር።  

ሀቅቼክ “ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትጋራው ድንበር አካባቢ ብዙ ወታደሮቿን አስፍራለች” የሚለውን ጽሁፍ ለመደገፍ የቀረበው ምስልን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።  

Similar Posts