ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም አንድ የፌስቡክ ገፅ “በአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ ጦር የተማረኩ የጣልያን ወታደሮች” በሚል የፅሁፍ መግለጫ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ300 ጊዜ በላይ መጋራት ሲችል ከ አንድ ሺህ በላይ ግብረ መልስ ማግኘትም ችሏል። ሀቅቼክ ይህ ምስል የተካተተበት በመረጃ ማጣራት ፅሁፉን የዛሬ አመት ለንባብ አብቅቶ ነበር።

ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱ ያቀረበውን መረጃ ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

የአድዋ ጦርነት 1896 እአአ በጣልያን ወራሪ ኃይል እና በአጼ ሚኒሊክ በሚመራው በኢትዮጵያ ጦር መካከል የተደረገ ጦርነት ሲሆን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሚገኘው አድዋ ከተማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደተከናወነ ታሪክ ያሳያል። 

ወራሪው የጣልያን ጦር በኤርትራ በኩል ወደ ደቡብ አቅጣጫ ተጉዞ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ጥረት አድርጎ የነበረ ሲሆን በጀነራል ኦሬስት ባራቴሪ የሚመራውና ዘመናዊ መሳርያን የታጠቀው የጣልያን ጦር በአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን ሽንፈት ገጥሞታል። በጦርነቱም በቁጥር የበዙ የጣልያን ወታደሮችና ከጣልያኖች ጋር ሲሰሩ የነበሩ ቅጥረኛ ወታደሮች አብዛኞቹ ሲገደሉ የቀሩት ተማርከዋል።   

ይህ የፌስቡክ ፖስት የተጋራው 81ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን ከሚከበርበት ከሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ሁለት ቀናት በፊት ነበር። በየአመቱ ሚያዝያ 27 ቀን የሚከበረው የአርበኞች ቀን መታሰቢያነቱ ሚያዝያ 27 ፤ 1933 ዓ.ም የጣልያን ወረራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃበትን እና የንጉስ አጼ ስላሴን ከስደት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ለመዘከር የሚከበር ብሄራዊ በዓል ነው። 

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ወቅት እና ሁኔታ በመጠቀም በአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ ሰራዊት የተማረኩ የጣልያን ወታደሮች በማለት ምስሉን ሊያጋራ ችሏል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የፌስቡክ ገፁ የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ምስሉ በጦርነቱ ወቅት በኢትዮጵያ ወታደሮች የተማረኩ የጣልያን ወታደሮችን እንደማያሳይ አረጋግጧል።

ምስሉ የተወሰደው በሚያዝያ ወር 1937 ዓ.ም አካባቢ በነበረ ሁነት ሲሆን ኢንሳይክሎፒድያን ጨምሮ የተለያዩ ድረ-ገፆች ላይ ይገኛል።

ምስሉ በመጀመሪያ በቀረበበት ድረ-ገፅ እንደተገለፀው ምስሉ የሚያሳየው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በጀርመን ጫካዎች ውስጥ የተማረኩ የናዚ ወታደሮችን ሲሆን የአሜሪካ የ12ኛ ክፍለ ጦር አባል የሆነ አንድ ወታደር እነዚህን የጀርመን ወታደሮች ሲጠብቃቸው የሚያሳይ ምስል እንደሆነ ይናገራል። 

ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ገፁ የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል።       

Similar Posts