ከ290 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ “የህዳሴ ግድቡ ንብረት አመላላሽ የነበሩ ሰራተኞች በጉዞ ላይ እያሉ በጉሙዝ ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል” የሚል ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከ10 ሺህ ጊዜ በላይ ግብረመልስ ያገኘ ሲሆን ከ1200 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ እስከ 6450 ሜጋዋት ሃይል ያመነጫል። ግድቡ ከሱዳን በስተምስራቅ 48 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በምትገኘው ጉባ ላይ እየተገነባ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።   

በየካቲት 23 ፤ 2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ የኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ እንደተናገሩት የጸጥታ ሀይሎች በቤንሻንጉል ክልል በህዳሴ ግድቡ አቅራቢያ ከቤንሻንጉል ክልል አማጽያን ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።”

የተለያዩ የዜና ምንጮችም በግጭቱ 13 የሚሆኑ የአማጽያኑ አባላት እንደተገደሉ አስነብበዋል። አማጽያኖቹ የተለያዩ ፈንጂዎችን ፣ ቦምቦች እና ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችን ይዘው እንደነበረ የሚያሳዩ የተለያዩ ሪፖርቶች አሉ። 

በሚያዝያ 7 ፤ 2009 ዓ.ም ብዙ ቢልየን ዶላሮች ፈሰስ በተደረገበት በዚህ ግዙፍ የውሃ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አካባቢ ጥቃት ፈጽመው በነበሩት 10 የሚደርሱ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ንቅናቄ አማጽያን ላይ ፍርድ ቤት ብይን ሰቷል። 

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሀሳብ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። 

ሀቅቼክ ይህ የፌስቡክ ፖስት የተጠቀመውን ምስል በተለያዩ ፅሁፎች ላይ አግኝቶታል። ለምሳሌ ይህ ምስል በነሃሴ 26 ፤ 2009 ዓ.ም International Business Times  በተባለ ድረ-ገፅ ላይ የ26 ዓመቱ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ክሪስቶፈር አለን ደቡብ ሱዳን ውስጥ በነበረ ግጭት ምክንያት ተገድሎ መገኘቱን የሚያሳይ ጽሁፍ ይዞ ወቷል። 

ምስሉም በደቡብ ሱዳን ያሉ አማጽያንን የሚያሳይ ሲሆን እነሱም አብረው ከሚዋጉ ጓዶቻቸው ጋር ለመመሳሰል እንዲረዳቸው በጭንቅላታቸው ላይ ቀይ ጨርቅ እንደሚያስሩ ይህ ፅሁፍ ያስነብባል።     

የጉሙዝ ታጣቂዎች በግድቡ አቅራቢያ ጥቃትን እንደከፈቱ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ የፌስቡክ ገጾች ይህንኑ ምስል ተጠቅመዋል። 

ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ገጾቹ የተጠቀሙትን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

Similar Posts