ከ120 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ነሀሴ 28 ፤  2014 ዓ.ም ላይ “በራያ ግንባር ከጠላት የተማረከ 430 ክላሽንኮቭ እና 3 ዲሽቃ ፤ ጠላት የጥምር ጦሩ ብርቱ ክንድ መቋቋም ያልቻለው ሀይል እየተማረከ ነው” የሚል ፅሁፍ በማያያዝ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ ፅሁፍ ከአንድ ሺህ በላይ ግብረመልስ ሲያገኝ ከ150 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።  

ጥቅምት 24 ፤ 2013 ዓ.ም በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ግጭት ከተከሰተ በኋላ የፌደራል መንግስት ከሌሎች የክልል ልዩ ሀይል እና ሚሊሻዎች ጋር በመሆን ህወሓትን ከመቀሌ እና ከሌሎች የትግራይ ዋና ዋና ከተሞች ማስለቀቅ ችሎ ነበር።  

ይሁን እንጂ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ይህ ጦርነት ህወሓት ከመቀሌ እና ከሌሎች ዋና ዋና የትግራይ ከተሞች ከለቀቀ በኋላ የሽምቅ ውጊያን መጠቀሙን ተከትሎ ጦርነቱ ሊራዘም ችሏል።

ይህን ተከትሎ የፌደራሉ መንግስት በጊዜው ተቋቁሞ ከነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን ግንቦት ወር 2013 ዓም ላይ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም በማድረግ የመከላከያ ሰራዊቱን እና የክልል ልዩ ሀይል እና ሚሊሻዎችን ከትግራይ እና አካባቢው አስወጥቷል።

ይህን የፌደራሉ መንግስትን ውሳኔ ተከትሎ ህወሓት የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን መልሶ መቆጣጠር ችሎ ነበር። ከዚህ በመቀጠልም ህወሓት ጦሩን ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች አንቀሳቅሷል። ይህን ተከትሎ የህወሓት ሀይሎችም የአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞችን ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ መቃረብ ችለው ነበር።    

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች ጥምር ሀይሎች በህወሓት ጦር ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃን መውሰድ ከጀመሩ በኋላ የፌደራሉ መንግስት በህወሓት ሀይሎች ተይዘው የነበሩ የአፋር እና አማራ ክልል ቦታዎችን መልሶ መያዝ ችሏል። 

መጋቢት 15 ፤ 2014 ዓ.ም ላይ የፌደራሉ መንግስት ከህወሓት ጋር ያለውን ግጭት ለማቆም መወሰኑን ገልፆ ነበር። ህወሓትም በፌደራል መንግስት የተላለፈውን ይህን ውሳኔ እንደሚቀበል ገልፆ ነበር።

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማደራደር ከሶስተኛ ወግን ሀሳብ መቅረቡን ተከትሎ የሰላም እና የድርድር ጥረቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይህን ተከትሎም የቀድሞው የናይጄርያ ፕሬዝዳንት እና በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ሊደረግ የታሰበውን የድርድር እና የሰላም ውይይት እንዲያግዙ በአፍሪካ ህብረት ተሹመዋል።

ፕሬዝደንት ኦባሳንጆም የድርድር ሂደቱን ለማስጀመር በተደጋጋሚ በሁለቱ ወገኖች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።       

ነገር ግን ህወሓት በፕሬዝደንት ኦባሳንጆ የሰላም ድርድሩ ለመምራት መመረጣቸው ላይ እንደማያምንበት እና ከፊደራል መንግስቱ ጋር በሚደረገው የድርድር ሂደት ላይ ድርድሩን ለመምራት ብቁነታቸው ላይ ጥያቄ እንዳለው አስታውቋል። 

ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ታንክ እና ከባድ መሳሪያዎችንም ተጠቅሞ ነሀሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጥቃት እንደሰነዘረበት ሕወሃት ገልፆ በመጋቢት ወር በሁለቱ ሀይሎች መካከል ተደርጎ የነበረውን ስምምነት የፈደራል መንግስት እንዳፈረሰው አስታውቋል።

በተጨማሪም ነሀሴ 18 ፤ 2014 ዓ.ም የፌደራል መንግስት በደቡባዊ የትግራይ አቅጣጫ ጥቃት እንደከፈተባቸው ህወሃት ገልጿል። 

ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት ይህ በህወሓት የቀረበው ውንጀላ ሀሰት መሆኑን በመናገር ህወሓት ወደ አጎራባች ክልልሎች ለመንቀሳቀስ የሚያረገውን ሙከራ ለማስቆም የትኛውንም ወታደራዊ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል።   

ነሀሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የጦር ግንባሮች ድል እያስመዘገበ እንደሆነ ተናግሯል።

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሁኔታ መሰረት አድርጎ ተጋርቷል። 

ሀቅቼክ ምስሎቹን ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሎቹን በአማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን የዩቲዩብ ቻናል ላይ ጥር 25 ፤ 2014 ዓ.ም በቀረበ የዜና ቪድዮ ላይ አግኝቷቸዋል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የዩቲዩብ ቪድዮው ከ150ሺህ ጊዜ በላይ ታይቷል። 

የመጀመርያው ምስል በዜና ቪድዮው በ23ተኛ ደቂቃ ከ05 ሴኮንድ ላይ ይገኛል  

ሁለተኛው ምስል በዜና ቪድዮው በ22ተኛ ደቂቃ ከ57ተኛ ሴኮንድ ላይ ይገኛል

የዜና ቪድዮው፣ “በመከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ጥምር ሃይል አማካኝነት በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ላይ በተወሰደው ርምጃ ከ100 በላይ የሚሆኑ አባላቱ ተደምስሰዋል” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም በቪድዮው ተማረኩ ያላቸውን የሽብር ቡድኑን አባሎች ያሳያል። በዚህም መሰረት መረጃውን ለመደገፍ ከፖስቱ ጋር የተያያዙትን ምስሎች ሀቅቼክ ሀሰት ብሏቸዋል።

Similar Posts