ከ38 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገጽ በጥቅምት 21 ፤ 2014 ዓ.ም 3ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ የሚፈጅ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስልን የከሚሴ ህዝብ ለኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ሸኔ) አቀባበል ሲያደርግ የሚያሳይ በማለት አጋርቶ ነበር። በልጥፉ ላይ የተያያዘው ፅሁፍ “ከሚሴ በአሁኑ ሰዓት የህዝብ ማዕበል እየታየ ነው… ህዝቡ በሙሉ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ከተማዋን በማጥለቅለቅ ደስታውን እየገለፀ ይገኛል። በነጻነት ባንዲራችንም ከተማዋ ደምቃለች…” ሲል ይነበባል። በምስሉ ላይም የኦሮሞ ነጻነት ግምባር (ኦነግ) እና ኦነግ ሸኔ የሚጠቀሙበት ባንዲራ ይታያል። ተንቀሳቃሽ ምስሉ ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ6300 ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን ከ70 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ይሁን እንጂ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ወቅታዊ ሁኔታን የሚያሳይ ባለመሆኑ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚያዝያ 23 ፤ 2013 ዓ.ም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ሸኔ) እና ህወሓትን አሸባሪ ቡድኖች በማለት ፈርጇቸዋል። ነሀሴ 5 ሁለቱ ቡድኖች በጋራ ለመስራት ጥምረት መፍጠራቸውን ገልፀዋል። በትግራይ  ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አፋር እና አማራ አጎራባች አካባቢዎች ከተስፋፋ በኋላ የሕውሃት ጦር ደሴ እና ኮምቦልቻን ጨምሮ ወደተለያዩ ከተሞች መግባቱ ሲዘገብ ቆይቷል። በጥቅምት 22 ሸኔ ከአዲስ አበባ 335 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን የከሚሴ ከተማን መቀጣጠሩን የገለጸ ሲሆን የፌስቡክ ልጥፉም በዚህ ሃሳብ የተጋራ ነበር።   

ይሁን እንጂ ከተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በተወሰደ ስክሪን ሾት የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ መሰረት ተንቀሳቃሽ ምስሉ ከዚህ ቀደም በጥቅምት 13 ፤ 2011 ዓ.ም በፌስቡክ ላይ የተጋራ መሆኑን ለማወቅ ትችሏል። ምስሉ የት አካባቢ እንደተወሰደ ግልፅ ባይሆንም የተለጠፈበት ጊዜ ግን እንደሚያሳየው ከሀገር ውጪ የነበሩና የተለያዩ የፖሊቲካ ፓርቲዎች እና አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ጥሪ ከቀረበላቸው በኋላ በመስከረም 2010 ዓ.ም  የኦነግ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት አከባቢ የተወሰደ መሆኑን ያመለክታል። 

በሌላ በኩል ይህ ገጽ በህዳር 2013 ዓ.ም “DW International ድምጺ ወያኔ” በሚል ስም የተከፈተ እንደሆነ እና በኋላም በነሃሴ 27 ፤ 2013 ዓ.ም ስሙን አዋሽ ፖስት ወደሚል ሌላ ስም የቀየረ ሲሆን እንደዚህ አይነት የስም ለውጦች የገፁን አገልግሎት ወይም ጥቅም ለውጥ የሚያሳዩ እና አብዛኛውን ጊዜ ለማሳሳት የሚደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።

ከላይ በቀረቡት የተለያዩ ምክንያቶች መሰረት የከሚሴ ነዋሪዎች የሸኔ ሰራዊት ወደ ከተማዋ መግባቱን ተከትሎ ደስታቸውን ለመግለፅ ወጡ ተብሎ የቀረበው ተንቀሳቃሽ ምስል ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።   

Similar Posts