“ደስ የሚል ዜና፤ መከላከያ VTOL ድሮን ታጠቀ” የሚል  የፌስቡክ ልጥፍ መስከረም 27፣ 2014 ዓ.ም ትጋርቷል። መረጃውን ያሰራጨው ገፅ ከ69,000 በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን በልጥፉ ላይ አያይዞም “እነዚህ ድሮኖች ከራዳር ውጪ በመሆን ሞርታር ማስወንጨፍ የሚችሉ እና የጠላትን አቅጣጫ በማነፍነፍ ጥቃት ማድረስ የሚችሉ ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤት ናቸው” ሲል ይነበባል።

ይሁን እንጂ ልጥፉ ላይ ያለው መረጃ የተዛባ በመሆኑ እና ከልጥፉ ጋር የተያያዘው ምስል የተሳሳተ በመሆኑ ልጥፉ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።

በትግራይ ክልል ያለው ግጭት መቀጠሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አየር ሀየሉ ዘመናዊ ድሮኖችን መታጠቁን እና በጦርነቱ ላይ መጠቀሙን አስታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኢራን ድሮኖችን ታጥቋል የሚሉ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል።

በልጥፉ የተጠቀሱት VTOL ድሮኖች ምንድን ናቸው?

VTOL የሚለው ቃል ሲተነተን (Vertical take-off and landing) ወይም ወደ ከፍታ በቀጥታ ተነስተው ማረፍ የሚችሉ ማለት ነው።

እነዚህ ድሮኖች ሰው አልባ ሲሆኑ እንደ ሄሊኮፕተር አቀባዊ በሆነ አቅጣጫ ተነስተው አኮብኩበው መልሰው ወደምድር መመለስ የሚችሉ ናቸው። ከVTOL ሰው አልባ ድሮኖች መካከል መልቲኮፕተር (Multicopter) የሚባሉት አንዱ ናቸው።

መልቲኮፕተር (Multicopter) የሚባሉት እነዚህ የድሮን አይነቶች ቀለል ያሉ የድሮን አይነቶች ሲሆኑ የግፊት ሞተራቸውን በመጠቀም ፍጥነታቸውን በመጨመር እና በመቀነስ መቆጣጠር ይቻላል።

VTOL የሚባሉት የድሮን አይነቶች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት በማዕድን ቁፋሮ፤ በኮንስትራክሽን ስራ፣ በነዳጅ ማምረቻ ድርጅቶች፤ ለአከባቢ ጥናት እና ካርታ ስራ እንዲሁም ለደህንነት እና መከላከያ ስራዎች ነው። በዚህም የሰፋፊ ቦታዎችን ምስል ለመውሰድ፤ መልክዓ ምድራዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንዲሁም የአየር ላይ ክትትል ወይም ስለላ ለማድረግ ይጠቅማሉ። በአጠቃላይ እነዚህ ሰው አልባ ድሮኖች በአይነቶቻቸው መሰረት ለተለያየ አላማ ይውላሉ።

ከላይ በቀረበው ጥቂት ገለፃ መሰረት እነዚህ VTOL ድሮኖች በፌስቡክ ልጥፉ እንደተገለፀው ከራዳር ውጪ በመሆን ሞርታሮችን ማስወንጨፍ የሚችሉ እንዳልሆኑ ተረድተናል። ይህም የፌስቡክ ልጥፉን ሀሰት ያደርገዋል።

በተጨማሪም በፌስቡክ ልጥፉ ላይ በተያያዙት ምስሎች ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ መሰረት ምስሎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቁት በሕዳር 15፣ 2011 ዓ.ም ዢኑዋ (Xinhua) በተባለ የዜና አውታር ላይ ነበር። የዜና ዘገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በቻይና ቤጂንግ በተዘጋጀው የድሮን ማብረር ስልጠና ላይ እንደተሳተፉ ዘግቧል።

ከዚህም ባሻገር የልጥፉን ሀሰተኛነት ከሚያሳዩት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላቱ የለበሱት ልብስ አሁን የተቀየረው እና ከ2012 ዓ.ም በፊት ሰራዊቱ ሲጠቀምበት የነበረው የደንብ ልብስ መሆኑ ነው።

ስለሆነም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት VTOL የተባሉ ከራዳር ውጪ በመሆን ሞርታሮችን መተኮስ የሚችሉ ድሮኖችን ታጥቋል የሚለው መረጃ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።

Similar Posts