ከ500 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ሚያዚያ 28 ቀን፣ “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ደምቢ ዶሎን መቆጣጠሩን ገለፀ” የሚል የፅሁፍ መግለጫ ያለው አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። መረጃውንም ለመደገፍ ከተቀመጡ ሦስት ምስሎች መሀል በአንደኛው ላይ “ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ” በሚል በቀይ ቀለም ተፅፎበታል።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ3ሺ በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ 950 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።

ቢሆንም ሀቅቼክ በቀይ ቀለም “ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ” ተብሎ የተፃፈበትን ምስል ለማጣራት ባደረገው ምርመራ ምስሉ ደምቢዶሎ ዩንቨርሲቲን እንደማያሳይ አረጋግጧል።

ይህም በመሆኑ ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል ትክክለኛነት አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሰራዊት፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የነበረ ሲሆን ሚያዚያ 23 ፣ 2013 ዓ.ም ለሁለት ተከፍሏል። በኢትዮጲያ መንግስት “ኦነግ ሸኔ” እየተባለ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሰራዊት በፓርላማ በአሸባሪነት ተፈርጇል።

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሰራዊት ከመንግስት ጋር በጦርነት ላይ ከሚገኘው ሕወሃት ጋር ጥምረት መፍጠሩን በነሀሴ 2012 አሳውቋል። 

የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር አቶ ለገሰ ቱሉ መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልልና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች በተቀናጀና ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኙ ገልፀዋል

በተጨማሪም መንግስት በምዕራብ ወለጋ በሚገኙት በነቀምት፣ በደምቢዶሎ እና በሌሎችም አከባቢዎች በኦነግ ሸኔ ላይ ጥቃት እየፈፀመ እንደሚገኝ የኮምኒኬሽን ሚኒስትሩ ገልፀዋል። 

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሁኔታ እና ወቅት በመጠቀም መረጃውን እንዲደግፍለት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሰራዊት በምዕራብ ወለጋ የሚገኘውን ደምቢዶሎ ከተማን መቆጣጠሩን ለማሳየት “ደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ” የሚል በምስል ላይ የተፃፈ ፅሁፍ አጋርቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የፌስቡክ ገፁ የተጠቀመውን ምስል ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ምርመራ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ በር የሚያሳየውን ምስል ከዚህ ቀደም ታህሳስ 12 ቀን 2010 ዓ.ም ላይ በቢቢሲ አማርኛ ዜና ‘በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ተማሪዎች ሞቱ’ በሚል ተጋርቶ አግኝቶታል። 

ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ገፁ የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts