አንድ የፌስቡክ ልጥፍ “በአዲስ አበባ በፍተሻ በአንድ ቤት የተገኘ ነው” በማለት ብዛት ያለቸው ጥይቶችን የሚያሳዩ ሁለት ምስሎችን በህዳር 7 ፤ 2014 ዓ.ም አጋርቶ ነበር። ይህ የፌስቡክ ገፅ ከ 411 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን 5000 የሚጠጋ ግብረመልስ አግኝቶ ከ690 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን በማጣራት ሀሰት ብሎታል። 

  

በሀገሪቷ በሰሜናዊ እና ሰሜናዊ ምስራቅ አካባቢ የተቀሰቀሰው ግጭት መስፋፋቱን ተከትሎ በሀገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በሚል የሰዓት እላፊ ተግባራዊ ተደርጓል። የፌደራሉ መንግስት እና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ እና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱ ባፋጣኝ ለፀጥታ ሃይሎች እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀርቧል። 

በቅርቡ ፖሊስ እና የፀጥታ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ለሽብር ተግባር ሊውሉ ነበሩ ያላቸውን የተለያዩ መሳሪያዎችን እና ተተኳሽ ጥይቶችን መያዙን ሪፖርት አድርጓል።   

ይህ የፌስቡክ ልጥፍም በዚህ ሁኔታዎች መሰረት በአዲስ አበባ ውስጥ በተደረገ ፍተሻ የተገኙ ጥይቶች በማለት አንድ ምስልን የተጠቀመ ቢሆንም ሀቅቼክ ምስሉ ከ8 ወር በፊት የተወሰደ እንደሆነ አረጋግጧል። 

በልጥፉ ላይ የተመለከተው የመጀመሪያው ምስል በሚያዚያ 7 ፤ 2013 ዓ.ም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኦሮምኛ ገጽ ላይ ከተፃፈ ጽሁፍ የተወሰደ ሲሆን ምስሉ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮምቦልቻ ኬላ ላይ የተያዙ ጥይቶችን ያሳያል። ትክክለኛውን ምስልን እዚህ ማግኘት ይችላሉ።  

የፌስቡክ ልጥፉን ለመደገፍ የተወሰደው ሁለተኛው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በሚያዚያ 8 ፤ 2013 ዓ.ም በአንድ የፌስቡክ ልጥፍ ላይ ሲሆን ልጥፉ አያይዞም ሁለት ግለሰቦች በኮምቦልቻ ከ5000 ከሚበልጡ ጥይቶች ጋር እንደተያዙ ይገልጻል። ትክክለኛው የፌስቡክ ልጥፍ እዚህ ይገኛል። 

ስለዚህ ሀቅቼክ በፌስቡክ ልጥፉ ላይ የተመለከቱት ምስሎች በቅርቡ በአዲስ አበባ የተያዙ ጥይቶችን የማያሳዩ በመሆናቸው ሀሰት ብሎታል።      

Similar Posts