Tigray people’s Liberation Front /TPLF/ የተባለ በፌስቡክ ማረጋገጫን ያገኘ እና ከ600 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገጽ “ጀግናው የትግራይ ሰራዊት ዛሬ ጠዋት በሚሌ ግንባር አንድ የወታደራዊ ሄሊኮፕተርን መቶ ጥሏል” በማለት የሚነድ የሄሊኮፕተርን የሚያሳይ ምስል በማያያዝ አንድ ልጥፍ አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ልጥፉ ከ650 ጊዜ በላይ ሲጋራ ከ6ሺህ በላይ ግብረመልስን አግኝቷል።   

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ አሁን በሃገሪቷ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ተመቶ የወደቀን ሄሊኮፕተር እንደማያሳይ በማረጋገጥ ሀሰት ብሎታል። 

ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ የህወሓት ሃይሎችና የኢትዮጵያው ፌደራል መንግስት አመት የፈጀ ጦርነት ላይ ይገኛሉ። ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ላይ የሕወሃት ባለስልጣናትን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመከላከያ ሰራዊትን ወደ ትግራይ የላኩ ቢሆንም በሰኔ ወር ሕወኃት የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችን ተቆጣጥሯል። 

በቅርቡም ጦርነቱ እየተስፋፋ የሄደ ሲሆን ሕወኃት ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች በመግባት ጥቃት እንደፈጸመ ሪፖርት ተደርጓል። የተለያዩ የሚዲያ ምንጮች የሕወኃት ሃይሎች አዲስ አበባን ለመቆጣጠር በመቃረብ ላይ እንደሚገኙና የፌደራል እና የክልል ሃይሎችን እያሸነፉ እንደሆነም እየዘገቡ ይገኛሉ።

የተለያዩ ቁልፍ ቦታዎችን በመቆጣጠር የፌደራሉን መንግስት ማዳከም ለሕወኃት ሃይሎች እንደወሳኝ ነገር የሚታይ ነው። በዚህ ጽሁፍ መሰረት በአፋር ክልል የምትገኘው የሚሌ ከተማ ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝኝ ዋና መንገድ እንደመሆኗ እሱን አካባቢ መቆጥጠር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋን የተጠቀመ ሲሆን ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው በጥቅምት 13 ፤ 2009 ዓ.ም “i was blown up and trapped by isis guns” በሚል ርዕስ  The Times በሚባል ድህረ ገጽ ላይ ነበር።    

ትክክለኛው ምስል 

ስለዚህ ሀቅቼክ ምስሉ በሚሌ ግንባር በህወሓት ሃይሎች ተመቶ የወደቀን ሄሊኮፕተር እንደማያሳይ ያረጋገጠ ሲሆን ይልቁንም ምስሉ ጦርነቱ ከመጀመሩ ከአራት አመት በፊት የተወሰደ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች መሰረት ልጥፉ ምስሉ ይገልጸዋል ከተባለው ነገር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ስለሌለው ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።   

Similar Posts