ከ 2 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ መጋቢት 26 ቀን፣ “በህገወጥ የሚወረረው ቦታ እያለቀ ሲመጣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የወጣቶች ማዘውተርያ የሆኑ ሜዳዎችን ለገበሬ በሚል ሰበብ ለልዩ ጥቅመኞች እየታደለ ነው። ይሄ ሀያት አካባቢ ልጆች ሲጫወቱበት የነበረ ሜዳ ነው በንጋታው ሲመጡ ታርሶ ጠብቋቸዋል” የሚል የፅሁፍ መግለጫ ያለው አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።  

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ1500 በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ 156 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።

ነገር ግን የፌስቡክ ፖስቱ ፅሁፉን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል ትክክለኛነት አጣርቶ ሀሰት ሀቅቼክ ብሎታል።    

የቅርብ መረጃዎች በአዲስ አበባ ከተማ መጠነ ሰፊ ህገወጥ የመሬት ወረራ እንዳለ የጠቆሙ ሲሆን፤ በቃሊቲ ፣ በለሚ ኩራ፣ በቦሌ እና በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች ላይ በስፋት መስተዋሉንም ገልፀዋል።

በአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ የሰራው ጥናት ግኝቶች መሰረት የመሬት ወረራው ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች “ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶች በመሆናቸው በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል” የሚሉ ግለሰቦች እና ወረራ በተፈፀመባቸው ቦታዎች አካባቢ የሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች አንደሆኑ በመጥቀስ ፣ “ጉዳዩን በማፋጠን ሕገ-ወጥ ደላላዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ” ብሏል።

በፌስቡክ ገፁ የቀረበው መረጃም ይህን ሁኔታ መሰረት አድርጎ የቀረበ ነው። 

ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት ጥረት ያደረገ ሲሆን ምስሉ ከዚህ ቀደም ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም “አዲስ አበባ የእግር ኳስ ሜዳዎቿ በ “ባለ ጊዜ ነን” ባዮች ወደ እርሻ ማሳነት እየተቀየሩ ነው” በሚል ርዕስ የወጣ ፅሁፍ አካል ሆኖ አግኝቶታል። 

ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱ ፅሁፉን ለመደገፍ የተጠቀመው ምስል የቆየ እና ከመረጃው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን አረጋግጧል።

ይህም በመሆኑ የፌስቡክ ፖስቱ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል አጣርቶ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።  

Similar Posts