አንድ የፌስቡክ አካውንት የተራራ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ እና መስራች የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከእስር ተፈቷል በማለት የካቲት 8 ፤ 2014 ዓ.ም አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።

ጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ የሚያሳየው ይህ ከፖስቱ ጋር የሚዘዋወረው ምስል፣ “ወንድማችን ዮናስ ወልደየስ እንዳሳወቀን ታምራት ነገራ ከእስር ተፈቷል። ሰዎች ያለጥፋታቸው መታሰር መቆም አለበት” በሚል መግለጫ ተጋርቷል።

 

ታምራት ነገራ በታህሳስ 1 ፤ 2014 ዓ.ም ከቤቱ በድንገት ተወስዶ ከታሰረ በኋላ ለሳምንት ያክል ያለበት ቦታ አልታወቀም ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ታህሳስ 7 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረብ ችሏል።  

እስሩን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጋዜጠኛውን ኦሮሚያ ክልል ወደሚገኘው የገላን ፖሊስ ጣቢያ አዘዋውሮታል።   

በመጨረሻም የጋዜጠኛው ጉዳይ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲሸጋገር በፍርድ ቤቱ በመወሰኑ ሌላ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳያስፈልግ ሆኗል። 

በየካቲት 8 ፤ 2014 ዓ.ም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህዳር ወር ላይ ታውጆ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቷል።  

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል

ይህ መረጃም ይህን ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ፖስት የተደረገው በነሃሴ 1 ፤ 2013 ዓ.ም ታምራት ነገራ በሚል  አንድ የፌስቡክ አካውንት ላይ ነበር።

ከዚያም በኋላ ይህ ምስል በቅርቡ በየካቲት 7 ፤ 2014 ዓ.ም “ነገ በተጠራው ልዩ የፓርላማ ስብሰባ SOE የሚነሳ ከሆነ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ጨምሮ ሌሎች በአዋጁ ምክንያት የታሰሩ በሙሉ ከእስር ይለቀቃሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለው።” በሚል ትዊት ላይ ተጋርቶ ነበር። 

በተጨማሪም ሀቅቼክ የታምራት ነገራን ቤተሰብ ደውሎ ያነጋገረ ሲሆን ጋዜጠኛው እስካሁን ከእስር እንዳልተፈታ ማረጋገጥ ችሏል። 

ይህም በመሆኑ፣ ታምራት ነገራ እንደተፈታ ተደርጎ የቀረበውን የፌስቡክ ፖስት ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።   

Similar Posts