ከ39ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ህዳር 26 ፤ 2015 ዓ.ም ላይ “ይህ ፊልም አይደለም እዚሁ ሀገራችን ውስጥ ነው” የሚል ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ260 በላይ ግብረ-መልስን ሲያገኝ ከ60 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ የቆየ እና በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ በማረጋገጥ ምስሉን ሀሰት ብሎታል።

ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው ከ8 ዓመት በፊት መስከረም 26 ፤ 2007 ዓ.ም ላይ በአንድ የትዊተር አካውንት ላይ ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በተለያዩ የእርስ በርስ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። ውስጣዊ የድንበር ግጭቶች ፤ የብሄር ግጭት ፤ ሞት እና መፈናቀሎችም ተከስተዋል።

ከነዚህ ክስተቶች መሃልም በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ተከስቶ የነበረው እና ለሁለት አመት ቆይቶ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ይጠቀሳል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ውስጥ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በተደጋጋሚ የተለያዩ የጅምላ ግድያዎች ፤ ሞት እና መፈናቀሎች እየተሰሙ ይገኛሉ።

አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው የሀገር ውስጥ ጋዜጣ ህዳር 24 ፤ 2015 ዓ.ም ይዞ በወጣው ዘገባ መሰረት ህዳር 16 እና ህዳር 20 በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ዞን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአማራ ፋኖ እና ሚሊሽያ ታጣቂዎች አማካኝነት እንደተገደሉ የሚያሳይ አንድ የዜና ሪፖርት ይዞ ወጥቷል።

በዚህ የፌስቡክ ገፅ ላይ የተጋራው ይህ መረጃም በዚህ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ የተጋራ ነው።

ስለዚህ ሀቅቼክ መረጃውን ለመደገፍ የተጋራውን ምስል መርምሮ ምስሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈፀመ እንዳልሆነ አረጋግጧል።

ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መስከረም 26 ፤ 2007 ዓ.ም በአንድ የትዊተር አካውንት ላይ ሲሆን “የህግ የበላይነት የታለ?” ከሚል የጥያቄ ፅሁፍ ጋር ተጋርቶ ነበር።

ይህን መረጃ ያጋራው የትዊተር አካውንት ከ30ሺህ በላይ ተከታይ ያለው ሲሆን አዳዲስ መረጃዎችን ከአፍሪካዊቷ ሀገር ማላዊ የሚያቀርብ እንደሆነ ይናገራል።

በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ ይህ የፌስቡክ ገፅ መረጃውን ይደግፍልኛል ብሎ የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts