ከደመራ በዓል ጋር ተያይዞ ይህች ህጻን አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ጥለት ያለው ቀሚስ ለብሳለች በሚል ከወላጆቿ ተነጥቃ በፌደራል ፖሊሶች ለ 10 ሰአታት ታግታለች በሚል የፅሁፍ መግለጫ አንድ የፌስቡክ አካውንት ይህንን ምስል አጋርቶት ነበር። ምስሉም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው መሰራጨት ችሎ ነበር። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ የቆየና እና ከዚህ በፊት የተጋራ መሆኑን አረጋግጧል። ምስሉም  በደመራ በዓል ላይ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ጥለት ያለው ቀሚስ ለብሳ በመገኘቷ ከወላጆቿ የተነጠቀች ልጅን አያሳይም፡፡ 

እንደ ጎርጎሮስያውያኑ አቆጣጠር በ1995 የወጣው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሶስት አግድም ሰንሰለቶች አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀይ ሲሆኑ በሰማያዊ መደብ ላይ ኮከብ ያረፈበት ነው።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተለይ በኮከብ አርማ አጠቃቀም  የግጭት፣ የአለመግባባትና የክርክር ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንድ ሰዎች የቀይ፣ ቢጫ እና አረንጓዴ ቀለም ባንዲራ ያለ የኮከብ አርማ ሲፈልጉ ሌሎች ደግሞ ይፋዊውን የኮከብ አርማ ይፈልጋሉ። የኮከብ አርማውን የማይፈልጉት ደግሞ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የተለያዩ ቡድኖች እና ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ይጻረራሉ ተብለው ይተቻሉ።

በደመራ በዓል አከባበር ላይ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ የኢፌድሪ  መንግስት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የቤተክርስትያኗን ምልክት ካላቸው ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ሰንደቅ አላማ ውጪ ምንም አይነት እውቅና የሌለውን ባንዲራ እና ምልክት ለብሰው በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ እንዳይመጡ አስጠንቅቀዋል። .

በበዓሉ ላይ ሰዎች ከደመራ በዓል ወይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማይወክሉ ሰንደቅ ዓላማዎች ወይም ምልክቶች ይዘው እንዳይመጡና መንግሥት ያወጣውን መመሪያ ማክበር እንዳለባቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።

ይህን ተከትሎ በደመራ በዓል ላይ አንድ ልጅ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ጥለት ያለው ቀሚስ ስለበሰች ከወላጆቿ ተነጥቃ በፌደራል ፖሊሶች ተወስዳለች በማለት በማህበራዊ ሚድያ ላይ ይህ ምስል ተጋርቷል።

ሀቅቼክ ይህን ፖስት መርምሮ ምስሉ የቅርብ ጊዜ እንዳልሆነ እና ተያይዞ የቀረበውን ሃሳብ የማይደግፍ መሆኑን አረጋግጧል።

በፖስቱ ላይ የሚታየው ምስል ከዚህ በፊት እ.አ.አ በጥር 2022 ትዊተር ላይ የተለጠፈ ሲሆን ምስሉ በመንግስት እና በህወሓት መካከል በተደረገው ጦርነት ወቅት የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በኢትዮጵያ በነበሩ ሰላማዊ ሰልፎች ጊዜ ተጋርቶ የነበረ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ሀቅቼክ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ትክክለኛ ስላልሆነ ልጥፉ ሐሰት ብሎታል።

ሀቅቼክ ለተጨማሪ መረጃ ምስሉን ያጋራውን ግለሰብ ለማግኘት የሞከረ ሲሆን ነገር ግን ግለሰቡ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።

Similar Posts