ከ274ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት “የትግራይ ቴሌቪዥን” ዩትዩብ ቻናል በጥቅምት 29 ፤ 2014 ዓ.ም “የፋሽሽቱ አብይ አህመድ መንግስት ድሮኖችን እና ከባባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም በወሎ ላይ የአየር ድብደባን ፈጽሟል” በማለት በትግርኛ የተፃፈ ርዕስን በመስጠት የዜና ቪዲዮ በመለጠፍ በጥቃቱም ብዙ ንጹሃኖች እንደተገደሉ ዘግቧል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የዩትዩብ ቪድዮው ከ73 ሺህ ጊዜ በላይ እይታን እና ከ1600 በላይ ግብረ መልሶችን ማግኘት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ትግራይ ቴሌቪዥን በዜና ዘገባው ላይ የተጠቀመውን ቪዲዮ አጣርቶ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።     

ከሕዳር 2013 ዓ.ም አንስቶ በህወኃት እና በኢትዮጵያ ፌደራሉ መንግስት መካከል ጦርነት እየተካሄደ ሲሆን በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አስወጥቷል።   

ከዚያም በኋላ የህወኃት ሃይሎች ወደ ደቡባዊ የክልሉ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ የአማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች ላይ ጥቃት ያደርሱ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የህወኃት ሃይሎች በአማራ ክልል የሚገኙትን የወሎ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ተሰምቷል።    

በሁለቱ ሃይሎች መካከል ባለው ጦርነትም ከጥቅምት ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተከታታይ የሆኑ የአየር ላይ ጥቃቶችን እያካሄደ ይገኛል። በዚህ ቪዲዮ ላይም በህወሃት የሚታገዘው ትግራይ ቴሌቪዥን ለማሳየት የሞከረው የኢትዮጵያ መንግስት በወሎ አካባቢ ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ የአየር ላይ ድብደባ አካሂዷል በማለት ነው።  

በትግራይ ቴሌቪዥን የተለቀቀው ቪዲዮ የፌደራሉ መንግስት ድሮኖችን ተጠቅሞ ወሎ ላይ ድብደባን ፈጽሟል የሚለውን ዜና ለመደገፍ ከ OMN (Oromia Media Network) ቲቪ ላይ የተደረገን ቃለ-ምልልስን እንደ ግብአት በመውሰድ ተጠቅመዋል።

ሀቅቼክ በOMN የተሰራዉን ቪዲዮ ማግኘት የቻለ ሲሆን ዜናው “ወሎ በብልጽግና አመራሮች ምክንያት በድሮኖች እና በከባባድ መሳሪያዎች እየተደበደበች እንደምትገኝ እና በዚህም ምክንያት ንጹሃንም ተጎድተዋል የሚል ነው።” በእለቱ ተጋባዥ እንግዳ የነበረችው ወ/ሮ ፋጡማ ኑሪዬ ለ OMN እንደተናገረችው በወሎ የሚገኘውና ለክርስትያን እና ለሙስሊም እንደ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቦታ ሆኖ የሚያገለግለው ጡርሲና ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በኢትዮጵያ አየር ሃይል እንደተደበደበ ገልጻለች። መረጃውን ለመደገፍ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪደዮ) አጋርቷል።

ሀቅቼክ ከቪዲዮው ላይ ስክሪን ሾት በመውሰድ ባደረገው ጉግል የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በጥቅምት 27 ፤ 2014 ዓ.ም በAFP News Agency የዩትዩብ ቻናል ላይ ሲሆን ቪዲዮው የሚያሳየው በሴራ ሊዮን፣ ፍሪታውን በመኪና አደጋ ምክንያት የተቀሰቀሰው እሳት ተስፋፍቶ እሳቱ ወደተለያዩ ቦታዎች በመሰራጨት ብዙ ጉዳቶችን ማድረሱን እና በአደጋው ቢያንስ 92 ሰዎች መሞታቸውን ነበር።

ምንም እንኳን በፌደራሉ መንግስት እና በህወኃት መካከል በአማራ ክልል እየቀጠለ ያለ ጦርነት ቢኖርም በትግራይ ቴሌቪዥን የታየው ቪዲዮ ግን በኢትዮጵያ አየር ሃይሎች የተደረገውን የድሮን እና የአየር ላይ ጥቃት ስለማያሳይ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።                                          

Similar Posts