ከ 194,424 በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ አካውንት በ ጥቅምት 12 ፣ 2014 ዓ.ም “ደሴ አሁን” በማለት አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። የፌስቡክ አካውንቱ ባለቤት እና የተሰጡት አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ምስሉ ከቀረበው ጽሁፍ ጋር ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ሕውሃት ከተማዋን እንደተቆጣጠራት ሲሆን ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ 700 ሰው በላይ ምላሽ ሲሰጥበት ከ 55 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል።

ይሁን እንጂ ምስሉ በጽሁፉ እንደተነበበው በጊዜው የነበረውን የደሴ ከተማ እንቅስቃሴን ስለማያሳይ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል። 

ካለፈው ዓመት  2012 ዓ.ም ጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕውሃት) ሃይሎች እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል እስካሁን የቀጠለን ጦርነት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊው አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ በመስማማት የመከላከያ  እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ አስወጥቷል። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ዜናዎች እና መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ። ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የፌደራሉ መንግስት ተደጋጋሚ የሆኑ የአየር ላይ ጥቃቶችን ማድረግ ጀምሯል። 

የሕውሃት ቃል አቀባይ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ እንደተናገረው ከሆነ የአየር ጥቃቱ የመኖሪያ ስፍራዎች ላይ ያነጣጠጠረ እንደነበረ ሲናገር መንግስት በበኩሉ የአየር ጥቃቱ በሕውሃት ሃይሎች ተይዞ በነበረ የወታደራዊ ካምፕ ላይ ኢላማ ያደረገ እንደነበር እና የሕውሃትን ክስ እንደማይቀበል ይናገራል። ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሕውሃት ሃይሎች አሁንም ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች በተለይም ወደ ወሎ አካባቢ ሃይሎቻቸውን እያስጠጉ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ደሴ በደቡብ ወሎ ዞን ከ አዲስ አበባ 400 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን በውስጧ ከ 200,000 በላይ ህዝብን ይዛለች። ከከተማዋ ፖለቲካዊ እና ስታራቴጂካዊ ጥቅም አንጻር ለሕውሃት ወደ ወሎ ለሚያደርገው ጉዞ ደሴ እንደ ቁልፍ ቦታ ሆና ትታያለች።

ትክክለኛው ምስል 

ይህ የፌስቡክ ልጥፍ በእነዚህ ሁኔታዎች መካከል የተነበበ ጽሁፍ ይሁን እንጂ በተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ መሰረት ምስሉ ጦርነቱ ከ ሶስት አመት በፊት በ ጥር 3 ፣ 2011 ዓ.ም የተለጠፈ እና ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞም የነበረ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ልጥፉ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።      

Similar Posts