ከ180 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መሪ ጃል መሮ ጦሩን ወደ አዲስ አበባ እንዲንቀሳቀሱ ካዘዛቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ ጉዟቸውን ጀምረዋል” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር። ልጥፉ ከ1000 በላይ ግብረመልስ ያገኘ ሲሆን ከ100 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት  መሆኑን አረጋግጧል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የነበረ እና የኦሮሞ ብሄረሰብን የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለማስጠበቅ አላማው አድርጎ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን የተመሰረተውም በ 1963 ዓ.ም ነበር።  በ 2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በሽብርተኝነት የተፈረጁና ከሃገር የተሰደዱ ፖለቲከኞች እንዲሁም የተለያዩ የፖሊቲካ ፓርቲዎች በ2011 ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዋር ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተደርጓል። 

ከዚያም በኋላ የኦሮሚያ ነጻነት ጦር ወይም ኦነግ ሸኔ የሚባል ስም መሰማት ጀመረ። የሸኔ ሰራዊት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ፣ ሰዎችን አፍኖ መውሰድ እና የመንግስት ባለስልጣናትን መግደልን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ወንጀሎችን ይፈፅማል ተብሎ ይወቀሳል። 

በሚያዚያ 23 ፤ 2013 ዓ.ም የኢ.ፌ.ድ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕውሃትን እና ኦነግ ሸኔን በሽብርተኝነት የፈረጃቸው ሲሆን በነሃሴ 5 ፤ 2013 ዓ.ም የኦነግ ሸኔ ጦር መሪ ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃል መሮ ጦራቸው ከሕውሃት ጦር ጋር አንድነት መፍጠሩን ለአሶሺየትድ ፕሬስ አሳውቋል። በጥቅምት 22 ፤ 2014 ዓ.ም የቢቢሲ አፍሪካ ዜና አጠናቃሪ የሆነችው ካትሪን ብያሩሃንጋ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሚስጥራዊ የጦር ቡድኖች” በማለት አንድ ቪዲዮ ሰርታለች ፤ በቪዲዮውም ቡድኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን ሲያደርግ የሚታይ ሲሆን ከቡድኑ መሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋ ነበር። በሪፖርቱም ጃል መሮ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ የሸኔ ጦር በደቡብ ፣ በምዕራብ እና መካከለኛው ኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞችን ተቆጣጥሯል ብሏል።

የፌስቡክ ልጥፉ በዚህ የተጋራ ሲሆን ሀቅቼክ የጎግል የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋን በመጠቀም ምስሎቹን አጣርቷል። ትክክለኛው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው በ ሐምሌ 6 ፣ 2013 ዓ.ም genevasolutions.news በሚባል አንድ የዜና ማሰራጫ ድህረ ገጽ ላይ ሲሆን “የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ባለው ግጭት ላይ ውሳኔ አሳልፏል” በሚል አርዕስት የተፃፈ ፅሁፍ ውስጥ ተያይዟል። ልጥፉም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል ለቆ እንዲወጣ እና ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በክልሉ የሚታዩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያሳስበው ገልጿል።

ይሁን እንጂ በፌስቡክ ልጥፉ ላይ የተመለከተው ምስል በፎቶሾፕ የተቀነባበረ እና ትክክለኛው ምስል ላይ ወታደሮችን በማድረግ የተሰራ ነው። 

የኦነግ ሸኔ ሰራዊት የተለያዩ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ ነው የሚሉ የተለያዩ ወሬዎች ቢኖሩም ምስሉ ግን ሀሰት እና የተቀነባበረ ስለሆነ ልጥፉ ሀሰት ነው።       

Similar Posts