ከ59 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ በጥቅምት 25 ፤ 2014 ዓ.ም ሁለት ምስሎችን አያይዞ ለጥፏል። ከልጥፉ ጋር ተያይዞ የተጻፈው ፅሁፍ “አካል ጉዳተኛ በመምሰል የስለላና የሰርጎ ገብነት ተግባር ሲፈጽሙ የተያዙ የወራሪው ሀይል አባሎች ናቸው…” የሚል ሲሆን ልጥፉ ከተለቀቀበት ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ420 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ መረጃውን አጣርቶ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።  

በጥቅምት 23 ፤ 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ክልል ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ፀጉረ ልውጦችን እንዲከታተሉ እና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱም ሪፖርት እንዲያረጉ የተለያዩ መልዕክቶች ሲተላለፉ ቆይቷል። ይህ ልጥፍም በዚህ ሀሳብ መሰረት ነው የተለጠፈው።

 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ዋናውን ምስል ማግኘት ችሏል። ምስሎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቁት የፌስቡክ ልጥፉ ከመጋራቱ ከ3 ሰዓታት በፊት በሃዲያ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዲፓርትመንት የፌስቡክ ገፅ ሲሆን ጥቅምት 24 ፤ 2014 ዓ.ም በሃዲያ ዞን ውስጥ አካል ጉዳተኛ በመምሰል ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሰዎች መያዛቸውን ለመዘገብ የተጋራ ነበር።       

 

ሀቅቼክ የሃዲያ ዞን ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባለሞያ የሆኑትን አቶ ይዲድያ ተስፋሁንን በስልክ አግኝቶ ያነጋገረ ሲሆን የፌስቡክ ገፁ ትክክለኛ የዞኑ ገፅ እንደሆነ እና ሁኔታውንም የዘገቡት እሳቸው መሆናቸውን አረጋግጠውልናል። 

ሀሰተኛ ምስሉ የተለጠፈበት የፌስቡክ ገጽ የተከፈተው በነሃሴ 17 ፤ 2013 ዓ.ም በታዋቂው የኢሳት ቲቪ ጋዜጠኛ ስም “መሳይ መኮንን – ኢሳት“ ተብሎ የተከፈተ ሲሆን በጥቅምት 2 ፤ 2014 ዓ.ም የፌስቡክ ስሙን ወደ “ክሊክ ደሴ” ቀይሮታል። የታዋቂ ሰዎችን ስም በመጠቀም የሚከፈቱ ግፆች ብዙ ተከታዮችን ለማፍራት እና የተዛባ መረጃን ለማሰራጨት አንዱ መንገድ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ እንደዚህ አይነት የስም ለውጦች የገጹን ተለዋዋጭ የሆነ አቋም የሚያሳዩ እና አብዛኛውን ጊዜ ለማሳሳት የሚደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።

ነዋሪዎች በየአካባቢያችው ፀጉረልውጦችን እንዲከታተሉ መንግስት መልዕክት ያስተላለፈ ቢሆንም በምስሉ ላይ የተመለከቱት ሰዎች ሰርጎ ገብ እና ሰላዮች አለመሆናቸው እና ልጥፉ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።       

Similar Posts