በታህሳስ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ አንድ የፌስቡክ ገፅ “ወላጅ ልጆቹን ትምህርት እንዲቀስሙለት ትምህርት ቤት ይልካል ባለ ጊዜ እንዲህ ያደርጋል” የሚል ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ400 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ በቅርቡ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ጋር ተነስቶ ከነበረው ግጭት ጋር የሚያያዝ እንዳልሆነ አረጋግጦ ምስሉን ሀሰት ብሎታል።  

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልላዊ መዝሙር እና የባንዲራ መሰቀል ጋር ተያይዞ በተማሪዎች እና በፀጥታ አካላት መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበር የሚያሳዩ አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ህዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋዊ የማህበራዊ ገፁ ላይ ባሰራጨው መረጃ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ አዳነች አቤቤ “በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን የሚሰሩ የግጭት ነጋዴዎችን በጋራ በመከላከል አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል እንዳሉ ያስነበበ ሲሆን ከንቲባዋ አያይዘውም ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በማያያዝ ግጭት ለመቀስቀስ የተሞከረው ጥረት የዚሁ አካል መሆኑንም ገልፀዋል።” 

ህዳር 29 ቀን 2015 ዓም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ ግጭትን ለመቀስቀስ እና ለማባባስ ሲሰሩ ነበሩ ያላቸውን 97 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።  

ፖሊስ በመግለጫውም ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተማሪ እና አስተማሪዎች የኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልል ባንዲራን ከተሰቀለበት በማውረድ ግጭትን ለማባባስ ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውንም ጨምሮ ገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሊድያ ግርማ በታህሳሰ 3  ቀን 2015 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ የፀጥታ ሀይሉ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ወስጥ ግጭትን ለመቀስቀስ አስበዋል ያላቸውን 72 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልፀዋል።     

ከዚህ በተጨማሪም ሀቅቼክ በታህሰሳ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አማራጮች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ልብስ የለበሱ የፀጥታ ሀይሎች በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የሚያሳዩ ቪድዮውች ሲዘዋወሩ ተመልክቷል። 

በዚህ ሳምንት የወጡ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የፌደራል መንግስት  በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኦሮምያ ክልል ባንዲራ እንዲሰቀልና መዝሙር እንዲዘመር እየተደረገ ያለው ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ እንዲቆም መመሪያ መስጠቱን ያሳያሉ። 

ይህ የፌስቡክ ፖስትም በነዚህ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ የተጋራ ነው።

ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሉን በ2009 ዓ.ም የሂዩማን ራይትስ ዎች ድረገፅን ጨምሮ በሌሎች ድረገፆች ላይ በ2009 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው የመንግስት ተቃውሞ  ላይ በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው አመፅ ምክንያት በኦሮሚያ የፀጥታ ሀይሎች የተያዙ ተማሪዎች ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ የሚያሳይ እንደሆነ በሚያሳይ የፅሁፍ መግለጫ ስር ተጋርቶ አግኝቶታል። 

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተማሪዎች እና በፀጥታ አካላት መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች ቢኖሩም ይህ የፌስቡክ ገፅ መረጃውን ይደግፍልኛል ብሎ ያጋራው ምስል የተሳሳተ ነው።በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።  

Similar Posts