ከ41ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገጽ በታህሳስ 1 ፤ 2014 ዓ.ም “የህውሃታውያንን ቁራሊዮ ናቸው ስንል አንድም ቀን አልተሳሳትንም። ይሄው የዘረፉትን ኮተት ይዘው ሲሄዱ ተይዘዋል…”። የሚል ገላጭ ጽሁፍ በመጠቀም አንድ ምስል አያይዞ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ ከ50 ጊዜ በላይ ሲጋራ ከ240በላይ ግብረ መልስ አግኝቷል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም አንስቶ በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ወታደራዊ ግጭት ቀጥሏል። በግንቦት 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ ሁሉንም የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ ዋና ዋና ቦታዎች አስወጥቷል። 

ከዚያ በኋላ የህወሓት ሃይሎች ራሳቸውን በማጠናከር ወደክልሉ ደቡባዊ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ አጎራባች በሆኑት የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በሕዳር 13 ፤ 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጦርነቱን በግምባር ሆነው ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ የተለያዩ የማጥቃት እና የመልሶ ማጥቃት የጦርነት ዜናዎች እየተሰሙ ይገኛልሉ። 

በህዳር 29 ፤ 2014 ዓ.ም የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኮምቦልቻ እና ደሴ አካባቢ ያሉ የእርዳታ ምግብ እና ቁሳቁስ መጋዘኖች በመዘረፋቸው የምግብ እርዳታ ስርጭት ማቆሙን ገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፈን ዱያሪክ በህዳር 29 ረቡዕ ዕለት በአማራ ክልል ኮምቦልቻ አካባቢ ብዛት ያለው ለዕርዳታ የሚውሉ የምግብ አቅርቦቶች እንዲሁም በምግብ ዕጥረት ለተጎዱ ህጻናት ሊሰራጭ የተዘጋጁ አልሚ ምግቦች መዘረፋቸውን አስታውቀዋል። 

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።    

ሀቅቼክ ምስሉን ለማጣራት የጎግል ተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋን የተጠቀመ ሲሆን ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው በጥር 8 ፤ 2011 ዓ.ም sapeople.com በተባለ ድህረ-ገጽ ላይ “SA Mentality? Over 1,600 Lives Lost on South Africa’s Roads Over Christmas Period” በሚል ርዕስ ስር በቀረበ ጽሁፍ ላይ ነበር። 

ከዚህ በተጨማሪ በፎቶሾፕ የተቀነባበሩ ምስሎችን ከምንለይባቸው መንገዶች አንዱ ምስሉን በትኩረት በመመልከት የተጋነኑ የቀለም ልዩነቶችን ፣ የምስሎቹ ጠርዝ መፈዘዝ ከታየበት ፣ ጥላ እና በግልጽ የሚታይ የመጠን ልዩነቶች ምስሉ የተቀነባበረ ለመሆኑ ማሳያ ሲሆኑ ይህም ምስል በፎቶሾፕ ለመቀነባበሩ እንደማሳያ መሆን የሚችለው የመኪናው የታርጋ ቁጥር የቀለም ግነት ነው።

 

ምንም እንኳን የህውሓት ሀይሎች በተለያዩ ከተሞች ዘረፋ እንደፈጸሙ ቢዘገብም  “የህወሓት ሃይሎች ያገኙትን እቃ እየጫኑ እየዘረፉ ነው” በማለት የተጋራው ምስል ሀሰት ነው። 

Similar Posts