በታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ ከ64 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገፅ “ወለጋ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የፈረጀውን  ኦነግ ሸኔን ለምን ተጋጠማችሁ ብሎ አማሮችን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ማሰር ጀምሯል።” የሚል የመግለጫ ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስል አያይዞ አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከ130 በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ30 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይሎች የአማራ ተወላጆችን ማሰር ጀምረዋል ተብሎ የተጋራው ምስል ትክክለኛነት አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

የፌደራሉ መንግስት እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው እና በሌሎች ደግሞ ኦነግ ሸኔ እየተባለ ከሚጠራው አካል ጋር ጦርነት ውስጥ እንደገባ የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ቆይቷል። በሁለቱ አካላት መካከል የተከሰተው ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየተስፋፋ መጥቷል። 

በዚህ ግጭት ምክንያት በኦሮሚያ ክልል በተለይም በወለጋ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል።  

የፌደራሉ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ተከታታይ የሆነ ግጭት እና ጦርነት ውስጥ እንደሆነ የሚያሳዩ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል። ይህ በዋነኝነት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አካባቢ በሁለቱ አካላቶች መካከል የተከሰተው ግጭት በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአጎራባች አካባቢዎችም ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ አለመረጋጋት ፣ የሰው ሞት እና መፈናቀልን እያመጣ ይገኛል።

የፌደራሉ መንግስት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል መንግስት በክልሉ ውስጥ ለሚፈጠሩ የሰው ልጅ ሞት እና መፈናቀሎች ተጠያቂው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ብለው ሲገልፁ በተቃራኒው ደግሞ ኦነግ ሸኔ ንፁሃን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ተጠያቂው እራሱ መንግስት ነው ሲል ሲከስ ይደመጣል

አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው የሀገር ውስጥ ጋዜጣ የአይን ምስክሮች ነገሩኝ ብሎ ባጋራው መረጃ መሰረት  በህዳር ቀን 16 እና 20 2015 ዓ.ም ላይ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ የአማራ ክልል ፋኖ ታጣቂዎች ብዙ ሰው መግደላቸውን ዘግቧል።  

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አካባቢ ግጭቶች የነበሩ ሲሆን የተከሰተው ግጭትም የብዙ ንፁሀንን ህይወት ቀጥፏል።  በዚህም ግጭት የተነሳ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጆች ከመኖሪያ ቦታቸው እንደተፈናቀሉ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡

በዚህ የፌስቡክ ገፅ ላይ የተሰራጨው ይህ መረጃም በዚህ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ ነው።

ሀቅቼክ መረጃውን ለመደገፍ የተጋራውን ምስል ለማጣራት ባደረገው ጥረት መሰረት ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው ሚያዝያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በቢቢሲ የኦሮምኛ ቋንቋ እትም ላይ ሲሆን በቢቢሲ ዘገባ መሰረት ምስሉ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን አብዶ አባ ጆቢር የተባለ መምህር በክልሉ ልዩ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉን የሚያሳይ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል።

በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts