ከ110ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት “ከሱዳን የጦር መሳሪያ ጭኖ በኤርትራ የአየር ክልል ወደትግራይ ክልል ሲበር የነበረ አንቶኖቭ አውሮፕላን በኤርትራ የአየር መቃወሚያዎች ዶግ አመድ ሆኖ ወደ መሬት ሲበተን” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ መጋቢት 7 ቀን ላይ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተከሰተው ግጭት ለብዙዎች መፈናቀል ፣ ሞት እና መሰደድ ምክንያት ሆኗል። 

ሕዳር 5 ቀን ፤ 2013 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሶስት ሮኬቶች እንደተተኮሱ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ።

ህዳር 24 ቀን ፤ 2014 ዓ.ም የሱዳን ሉዓላዊ ም/ቤት መሪ የሆኑት አብድልፈታ አልቡርሃን ከሱዳኑ አልሃዳት ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ የሱዳን መንግስት ህወሓትን እንደማይደግፍ የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ ወስዳብናለች ያሉትን መሬት በጦርነት ሳይሆን በውይይት እንደሚፈቱት ተናግረዋል።  

ይህ የትዊተር ፖስትም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበትን የእርስ በርስ ግጭት እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የውዝግብ መቼት መረጃውን ለመፍጠር ተጠቅሞበታል። 

ሀቅቼክ ምስሉን ለመመርመር ባደረገው ጥረት ፎቶውን በአንድ AEROPRESS BG በተባለ የዩቱብ ቻናል ላይ አግኝቶታል። ይህ የዩቱብ ቻናል ከ2ሺህ በላይ ሰብስክራይበሮች ያሉት ሲሆን፣ “የካርጎ ማመላለሻ የነበረው Boeing 747-400 በአፍጋኒስታን ውስጥ ተከስክሷል” የሚል ጽሁፍን አያይዞ በሚያዝያ 22 ፤ 2005 ዓ.ም ይህን ቪድዮ አጋርቶ ነበር።

እንደ Wikipedia መረጃ ከሆነ ይህ Boeing 747-400 የተባለው አውሮፕላን አሁንም ለጭነት ማመላለሻነት እያገለገለ ይገኛል። 

የዚህን ቪድዮ ዝርዝር መረጃን በሚያዝያ 24 ፤ 2005 ዓ.ም በ CNN  ቴሌቪሽን ላይ የሚገኝ ሲሆን እንደ CNN የዜና ሪፖርት መሰረት በአውሮፕላኑ የመከስከስ አደጋ ሰባት አሜሪካኖች ሲሞቱ ስድስቱ ከሚቺጋን አንዱ ከኬንታኪ የመጡ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ዜጎች መሆናቸው ተረጋግጧል። 

የመከስከሱ አደጋ የተፈጠረበት ቦታ በአፍጋኒስታን የሚገኝ እና ቤግራም የተባለ የአሜሪካ የአየር ሀይል ቤዝ ነበር። 

ይህ የትዊተር ፖስትም ምስሉን ከዚህ ቪድዮ ላይ ቆርጦ በመውሰድ ሊጠቀምበት ችሏል። ስለዚህ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።             

Similar Posts