በየካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም አንድ የትዊተር አካውንት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ውስጥ የተከሰተውን ድርቅ ያሳያል በማለት አንድ ምስልን አያይዞ አጋርቶ ነበር።
ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የትዊተር ፖስት ከ2ሺህ በላይ እይታን ማግኘት የቻለ ሲሆን ከ50 ጊዜ በላይ ደግሞ መጋራት ችሏል።
ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ በአሁኑን ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ድርቅ እንደማያሳይ በማረጋገጥ የትዊተር ፖስቱን ሀሰት ብሎታል።
የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኦሮሚያ እና የሶማልያ ክልል አካባቢዎች ላይ ከባድ ድርቅ መከሰቱን ያሳያሉ።
ይህ ድርቅ በእነዚህ አካባቢዎች ለአምስት ተከታታይ አመታት ተከስቷል። ይሁን እንጂ በነዚህ አካባቢዎች ከተከሰቱት ድርቆች መካከል በቦረና የተከሰትው ድርቅ ከባዱ ነው።
በምስራቃዊ እና ደቡባዊ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተለይም የቦረና አካባቢ ባለፉት አመታቶች ከባድ በሆነ ድርቅ የተጎዳ አካባቢ ነው። ከዚህ ድርቅ ጋር በተያያዘ በባለፈው አመት በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት ፤ ሴቶች እና አረጋውያን በምግብ እጥረት እና በድርቁ ምክንያት የቀንድ ከብቶቻቸውን በማጣታቸው ምክንያት ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋልጠው ነበር።
በአሁኑ ሰዓት በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ከአየር ንብረት መለዋወጥ እንዲሁም እነዚህ አካባቢዎች ዝናብ በማጣታቸው ምክንያት የተከሰተ ነው።
ይህ ድርቅ ወደ 800ሺህ የሚጠጉ የዞኑ ነዋሪዎችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል።
በኢትዮጵያ በምስራቁ ክፍል እና እንደ ቦረና ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ማለት በሚቻል መልኩ በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ ሲሆኑ ህልውናቸው በቀንድ ክብቶቻቸው ላይ የተመሰረተ ነው።
ይህ ለአምስት ተከታታይ አመታት የጠፋው ዝናብ የቦረና እና አካባቢው ነዋሪዎችን ህይወት አበላሽቷል።
በዚህ መረጃ ላይ ተመስርቶ ይህ የትዊተር አካውንት የሞቱ የቀንድ ከብቶችን ምስል በማያያዝ በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተውን ድርቅ ያሳያል በማለት አጋርቶት ነበር።
ይሁን እንጂ ምስሉ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በቦረና እና አካባቢው ያለውን ድርቅ አያሳይም።
ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ የፌስቡክ ገፅ ላይ ተጋርቶ ነበር።
በወቅቱ የተጋራው ይህ የፌስቡክ ፖስት በኦሮሚያ የባሌ እና ቦረና አካባቢዎች በድርቅ መጠቃታቸውን እንደሚያሳይ ከሚገልፅ ፅሁፍ ጋር ተጋርቶ ነበር።
ስለዚህ ሀቅቼክ በአሁኑ ወቅት በቦረና ዞን አስከፊ ድርቅ ቢኖርም ነገር ግን ይህ የትዊተር ፖስት የቆየ ምስልን በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት ብሎታል።