በታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ ከ20ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገፅ “በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ሚዥጋ ወረዳ መንደር 42/ተንካራ ላይ ታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ  ከአርጆ ጉደቱ በመነሳት ወረራ የፈጸመው መንግስት መሩ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና አሸባሪው ኦነግ ሸኔ ሰላማዊ አማራዎችን በጅምላ በማጥቃት መኖሪያ ቤቶችን እያቃጠለ እና እየዘረፈ ነው።”  የሚል የመግለጫ ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከ190 በላይ ግብረመልስን ሲያገኝ ከ30 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ይህ የፌስቡክ ፖስት መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

የፌደራሉ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከኦነግ ሸኔ ትጣቂዎች ጋር ተከታታይ የሆነ ግጭት እና ጦርነት ውስጥ እንደሆነ የሚያሳዩ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል። ይህ በዋነኝነት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አካባቢ በሁለቱ አካላቶች መካከል የተከሰተው ግጭት በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአጎራባች አካባቢዎችም ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ አለመረጋጋት ፣ የሰው ሞት እና መፈናቀል እየተፈጠረ ይገኛል።

የፌደራሉ መንግስት እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት በክልሉ ውስጥ ለሚፈጠሩ የሰው ልጅ ሞት እና መፈናቀል ተጠያቂው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ብለው ሲገልፁ በተቃራኒው ደግሞ ኦነግ ሸኔ ንፁሃን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ተጠያቂው እራሱ መንግስት ነው ሲል ሲከስ ይደመጣል

በቤንሻንጉል ክልል ካማሺ ዞን እና አካባቢው ተከታታይ የሆኑ ግጭት ፣ ሞት እና መፈናቀሎች ሲከሰቱ የቆዩ ሲሆን ይህ አካባቢም ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ጋር ድንበር እና ወሰኖችን ይጋራል።

 
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አካባቢ ግጭቶች የነበሩ ሲሆን የተከሰተው ግጭትም የብዙ ንፅሁንን ህይወት ቀጥፏል።  በዚህም ግጭት የተነሳ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጆች ከመኖሪያ ቦታቸው እንደተፈናቀሉ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡

በዚህ የፌስቡክ ገፅ ላይ የተሰራጨው ይህ መረጃም በዚህ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ የተጋራ ነው።

የፌስቡክ ገፁ በቤንሻንጉል ክልል ካማሺ ዞን ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይሎች ከኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጋር በመሆን የአማራ ተወላጆችን ቤት እያቃጠሉ ነው የሚለውን መረጃ ይደግፍልኛል በማለት አንድ ምስልን አያይዞ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ የፌስቡክ ገጽ እንደተናገረው ምስሉ ከኦሮሚያ ክልል በመጡ ታጣቂዎች አማካኝነት የሚቃጠል የአማራ ተወላጆች ቤቶችን አያሳይም።

ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሉን ታህሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ ከተጋራ አንድ ፅሁፍ ውስጥ አግኝቶታል። ይህ ምስል በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን ውስጥ በነበረው ግጭት ላይ የተቃጠሉ ቤቶችን እንደሚያሳይ ከሚገልፅ ፅሁፍ ጋር አብሮ ተጋርቷል።

በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts