ከ25ሺ በላይ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ላይ “ኦባሳንጆ ከታላቁ የፖለቲካ ልሂቅ ፕርፌሰር መራራ ጉዲና ጋርም ስለ ሰላም መክረዋል!” በሚል የፅሁፍ መግለጫ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የትዊተር ፖስቱ ከ150 በላይ ግብረ መልሶችን ሲያገኝ ከ35 ጊዜ በላይ ሪትዊት ተደርጓል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን ድረስ ያልተፈታ ችግር ሆኗል። 

ከጥቂት ወራት በፊት ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በሚል በፌደራሉ መንግስት የቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት በህወሓት ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ የነበረ ሲሆን ይህ ስምምነት ለሰላም ንግግር እና ግጭቱን ለማቆም ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተገምቶ ነበር። 

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ነሀሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም የምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው መሾማቸውን የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ አሳውቀዋል። የምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተወካዩም በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚሰሩ ይሆናል።

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከመንግስት ሀላፊዎችና ከህወሓት አመራሮች ጋር ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት በተደጋጋሚ ተገናኝተዋል። በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሁለቱም አካላት ጦርነት እንዲያቆሙና ወደ ድርድር እንዲመጡ ሀላፊነት ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ። 

ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋር በመቀሌ ከተማ ተገኝተው ተነጋግረዋል። ከሁለት ቀናት በኋላም ለስራ ጉብኝት ከጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ጋር ባሌ ሮቤ ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል። 

የትዊተር ፖስቱም ይህን አውድ ታሳቢ በማድረግ የተጋራ ነበር። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የፌስቡክ ገፁ የተጠቀመውን ምስል ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ምርመራ ምስሉ ከዚህ ቀደም የነበረና የቆየ  ሆኖ ያገኘው ሲሆን “የአፍሪካ ህብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን የበላይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ዶ/ር መራራ ጋር ተገናኝተዋል።”በሚል በአፍሪካ ህብረት ይፋዊ ድረ ገጽ ላይ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተጋርቶ አግኝቶታል። 

ስለዚህ ሀቅቼክ የቲዉተር ገፁ የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts