126ተኛው የአድዋ ድል በዓል በሚከበርበት የካቲት 23 ፤ 2014 ዓ.ም ቀን ላይ ከ46 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገጽ “ጨለንቆ ላይ የምኒሊክ አረመኔነት ታስቦ ውሏል” በሚል ጽሁፍ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።

ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከአንድ ሺህ በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ217 ጊዜ በላይ ደግሞ መጋራት ችሏል።

 ይሁን እንጂ ይህ የፌስቡክ ገጽ የተጠቀመው ምስል በ2007 ዓ.ም The Oromian Economist ከተባለ ድረ-ገጽ ላይ የተወስደ እንደሆነ ሀቅቼክ አረጋግጧል። 

126ተኛው የአድዋ ድል በዓል የካቲት 23 ቀን በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ውሏል። ይህ የአድዋ ድል የመታሰቢያ ቀን በመዲናዋ አዲስ አበባም በአድዋ ድልድይ እና ሚኒሊክ አደባባይ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሮ ውሏል። 

የኦሮሞ መብት ተከራካሪዎች አያሌ የኦሮሞ ሰማዕታት በጨለንቆ ጦርነት ላይ ለነፃነት ፣ ከጥገኝነት ለመላቀቅ ፣ ለፍትህ እና ለሰብዓዊነት እንደተዋደቁ ይናገራሉ። የጨለንቆ ጭፍጨፋ የመታሰቢያ ሀውልት ምርቃት የተከናወነው በመጋቢት 12 ፤ 2007 ዓ.ም በምስራቅ ሀረርጌ ነበር።

የጨለንቆ ጦርነት የተካሄደው በጥር ወር 1879 ዓ.ም በሸዋው ንጉስ አጼ ምኒልክ እና በሀረሩ ኢሚር አብደላህ ሁለተኛው መካከል ነበር። በጦርነቱ የሸዋው ንጉስ አጼ ሚኒሊክ  የሀረሩን ኢሚር አብደላ አሸንፈዋል። 

   

ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ እንዳረጋገጠው The Oromian Economist “በመጋቢት 12 ፤ 2007 ዓ.ም የጨለንቆ ጭፍጨፋ የመታሰቢያ ሀውልት ምረቃ” በሚል ርዕስ በቀረበ ፅሁፍ ውስጥ ይህን ምስል ተጠቅሞት ነበር። ይህ የዜና ሪፖርትም ከምርቃቱ ሁነት ላይ የነበሩ የተለያዩ ምስሎች እና ቪድዮዎችን አያይዞ አጋርቶ ነበር። 

በዚህም መስረት ያቀረበውን ሪፖርት ለመደገፍ የፌስቡክ ገጹ የተጠቀመበትን ምስል ወቅታዊነት አጣርቶ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።  

Similar Posts