ከ39ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ “ይህ በሻሸመኔ ቤተ እምነት ቅጥር ግቢ ውስጥ በፍተሻ የተገኘ ነው።” የሚል ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ13 ጊዜ በላይ መጋራት ችሎ ነበር።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ የቆየ እና ከዚህ መረጃ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አረጋግጧል። 


ስለዚህም ሀቅቼክ ይህን የፌስቡክ ፖስት ሀሰት ብሎታል።   

በጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሊቀ-ጳጳሳት ከቤተክርስትያኗ ሲኖዶስ እውቅና ውጭ የተለያዩ ጳጳሳትን ሾመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ እና ሁለት ሌሎች ጳጳሳት አንድ ላይ በመሆን ወደ 26 የሚጠጉ ኤጲስ-ቆጶሳትን በተለያዩ የኦሮሚያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሾመዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአቡነ ሳዊሮስ አማካኝነት ወደ 70 የሚጠጉ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ደብሮች ላይ ተመድበው ነበር።

ከዚህ ሁኔታ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባን በመጥራት ከቤተክርስትያኗ እውቅና ውጭ የተሾሙትን ጳጳሶች እና በሹመቱ ላይ የተሳተፉትን በሙሉ አውግዛለች።

ከዚህም በተጨማሪ የቤተክርስትያኗ ሲኖዶስ እነ አቡነ ሳዊሮስን እና ሌሎች ጳጳሳትን የቤተክርስትያኗን ቀኖና በመተላለፋቸው ምክንያት ከአባልነት አስወግዳቸዋለች።    

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከቤትክርስትያኗ ተለይተው የወጡት ሊቀጳጳሳትም በበኩላቸው ወደ 12 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሊቀጳጳሳትን በማውገዝ ከአባልነትም ማገዳቸውን አስታውቀው ነበር። 

ከቤትክርስትያኗ ተለይተው የወጡት ሊቀጳጳሳት መሪ የሆኑት አቡነ ሳዊሮስ አቡን ጳውሎስን የምዕራብ አርሲ ሀገረስብከት በሻሸመኔ ከተማ አመራር አድርገው መሾማቸው ይታወቃል። አዲስ የተሾሙት ጳጳስ ወደ ሻሸመኔ ከተማ ለመግባት መጓዛቸውን ተከትሎ በከተማዋ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል። 

እንደተለያዩ የዜና ሪፖርቶች ከሆነ በከተማዋ በተከሰተው ግጭት ወደ ሶስት የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።  

ይህ የፌስቡክ ፖስትም በዚህ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተጋራ ነው።

ሀቅቼክ መረጃውን ይደግፋሉ የተባሉትን ምስሎች ለማጣራት በደረገው ጥረት ምስሎቹ የቆዩ እና ከሁለት አመት በፊት ተጋርተው የነበሩ መሆናቸውን አረጋግጧል። 

ምስሉ ለመጀመርያ ጊዜ በመጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የፌስቡክ ገፅ ላይ “የፌደራል ፖሊስ በሲዳማ ከተማ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተከማችቶ የነበረ የጦር መሳርያ በቁጥጥር ስር ውሏል።” በሚል መግለጫ ተጋርቶ ነበር። 

በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱን ሀሰት ብሎታል። 

Similar Posts